የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት የትብብርና የቁርጠኝነት ማሳያ ነው ሲሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በህብረት እውን የሆነ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን መገለጫ ብሎም የመቻል ማሣያም ጭምር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ በብዙ ልፋትና መስዋዕትነት የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመስከረም ወር እንደሚመረቅ ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የጋራ ተጠቃሚነት አቋሟ የጸና መሆኑን መናገራቸውም እንዲሁ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአንድነት ታሪክ መስራት እንደሚቻል የተረጋገጠበት የትውልድ ተሻጋሪ የልማት ቱርፋት ነው፡፡
ሌተናል ኮሎኔል ደስታ ዳና በሰጡት አስተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሃብት የተገነባ፣ የሁሉም ሃብትና የዘመኑ ቅርስ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ያሳኩት የሀገር ሃብት መሆኑን ያነሱት ሌተናል ኮሎኔሉ ለህዳሴ ግድቡ እውን መሆን የሠራዊቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ሠራዊቱ ከግድቡ ጅማሮ እስካሁን ድረስ ቀን ከለሊት ደህንነቱን የማስጠበቅ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ብስራት መሆኑን ጠቁመው፤ የሠራዊቱ ገድል በተግባር የታየበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሻለቃ አስቻለው ኛኙኬ እንዳሉትም ግድቡ ለመከላከያ ሠራዊቱ ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ሠራዊቱ ግድቡ ዘወትር በንቃት እየጠበቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሠራዊቱ የደሙ አካል፤ የህይወቱ ዋስትና ነው ያሉት ሻለቃው የኢትዮጵያዊያን የህልውና መሠረት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የትውልዱ ዳግማዊ ዓድዋ ነው ያሉት ደግሞ ሻለቃ ስንታየሁ ለማ ናቸው፡፡
ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የሕብረት እና የይቻላል መንፈስ በተግባር የታየበት መሆኑን ገልጸው፤ የሁሉም አሻራ ያረፈበት የአንድነት አርማ መሆኑን መጠቆማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆሙ የማያሳኩት ነገር እንደሌለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህያው ምስክር መሆኑም ተጠቁሟል፡፡