ሎተሪ ደርሶናል በማለት የማታለል ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ/ም በአራዳ ክ/ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ቦታው መሀሙድ ሙዚቃ ቤት አካባቢ ነው፡፡
ተከሳሾች አቶ ታደለ አለጋ፣ ወ/ሮ የምስራች ወይም ስንታየሁ ስንዝሮ እና ወ/ሮ ጤናዬ መለሰ የተባሉ ሲሆን ወ/ሮ ሙልታዝም ሽኩር የተባሉ የግል ተበዳይን ሎተሪ ሳይወጣላቸው 75ሺህ ብር የደረሳቸው በማስመሰል ያዘጋጁትን ሀሰተኛ የሎተሪ ቲኬት በማሳየት መታወቂያ የሌለን በመሆኑ ገንዘቡን በግል ተበዳይ መታወቂያ እንድታወጣላቸውና ይህንንም ካደረገች ሠላሳ ሺህ ብር በስጦታ መልክ እንደሚሰጧት ይነግሯታል፡፡
የግል ተበዳይም በወቅቱ በሀሳባቸው በመስማማት የያዙትን ሎተሪ ስትቀበላቸው “ወደ ብሔራዊ ሎተሪ ለመግባት የሚያስፈልገው መታወቂያና 20 ብር ብቻ በመሆኑ የያዝሽውን ዕቃ ለእኛ ስጪን እዚሁ እንጠብቅሻለን” በማለት ግምቱ 15ሺህ ብር የሚያወጣ አንድ ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 14 ሺህ ብር የሚገመት አንድ ሳምሰንግ A15 ሞባይል ስልክ እና 10ሺህ ብር በካሽ ይቀበሏታል፡፡
የግለሰቦቹን ድርጊት በስውር ሆነው ሲከታተሉ የነበሩት ሲቪል ክትትል የፖሊስ አባላትም ተከሳሾች ከግል ተበዳይ አታለው የወሰዱትን ዕቃ በመያዝ ሊሰወሩ ሲሉ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው መቻላቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።
ህብረተሰቡ መሰል የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈፀምበት በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች የጥንቃቄ መልዕክቶች እየተላለፉ ቢገኙም አንዳንዶች አሁንም የእዚህ ወንጀል ሰለባ በመሆን ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም ህብረተሰቡ የሚሰጡ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን በመስማትና በመተግበር ራሱን ከመሰል የወንጀል ድርጊቶች መከላከል እንዳለበት ፖሊስ አሳስቧል።