የትውልደ ኢትዮጵያውያን እገዛ ለስኬት እንዳበቃት የምትናገረው ናኦሚ ግርማ

You are currently viewing የትውልደ ኢትዮጵያውያን እገዛ ለስኬት እንዳበቃት የምትናገረው ናኦሚ ግርማ

AMN – ነሃሴ 22/2017 ዓ.ም

ስሟ በሀገራችን ስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ ተደጋግሞ ተሰምቷል፡፡ በተለይ የዓለም የሴቶች ክብረወሰን ሰብራ ቼልሲን ስትቀላቀል ስለ እርሷ ለማወቅ የጓጉ በርካታ ናቸው፡፡

የእንግሊዝ የሴቶች ሱፐር ሊግ ተሳታፊ ለሆነው ቼልሲ በመጫወት ላይ የምትገኘው ናኦሚ ግርማ በጥር 2025 ያደረገችው ዝውውር በወቅቱ የዓለም ክብረወሰን ሆኖ ነበር፡፡ አንድ ሚሊየን ዶላር ተከፍሎባት ለቼልሲ የፈረመችው ናኦሚ ግርማ የተወለደችው ሳን ሆሴ ካሊፎርኒያ ነው፡፡ አባቷ ግርማ አወቀ እና እናቷ ሰብለ ደምሴም የተገናኙት በዛው ሳን ሆሴ ነው፡፡

አባቷ ግርማ አወቀ ለእግርኳስ ልዩ ፍቅር ያለው እና በሚኖርበት አካባቢም የትውልደ ኢትዮጵያን ልጆች የሚሰለጥኑበት ማለዳ የእግርኳስ ክለብ በሚል መመስረት ችሏል፡፡ ናኦሚ ግርማም በዛው ፕሮጀክት በአባቷ የመሰልጠን እድል አግኝታ የእግርኳስ ሕይወት መሰረቷን ጥላለች፡፡ በአባቷ እና ሌሎች አሰልጣኞች እገዛ እራሷን ያሳደገችው ኖኦሚ ግርማ በትምህርት ቤቷ የተመረጠች እግርኳስ ተጫዋች ሆነች፡፡ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ለተቋቋመው ’’ስታንፎርድ ካርዲናል’’ የሴቶች እግርኳስ ቡድን በተከላካይ ስፍራ በመጫወት የፕሮፌሽናል ሕይወቷን መሰረት አስይዛለች፡፡

በ2022 ሳንዲያጎ ዌቭን ተቀላቅላ ይበልጥ ለዓለም እግርኳስ አፍቃሪ እረሷን አስተዋወቀች፡፡ በጥር 2025 ደግሞ ለቼልሲ ፈርማ ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋገረች፡፡ ከ16 ዓመቷ ጀምሮ እትብቷ የተቀበረባትን ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በመወከል ተጫውታለች ፡፡ በ2022 ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ከመቀላቀሏ በፊት ከ17 ፣ ከ19 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን ወክላ ግልጋሎቷን ሰጥታለች፡፡

አሁን 25 ዓመቷ ላይ የምትገኘው ናኦሚ ግርማ ዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች እንደ አንዷ ትቆጠራለች፡፡ ለዚህ ስኬት የበቃሁት የቤተሰቦቼ ጥረት እንዳለ ሆኖ የትውልደ ኢትዮጵያውያን እገዛ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ባይ ናት፡፡ በቤተሰቦቿ የቅርብ ጓደኛ የተሰራው ባህላዊ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ሰላሜን የማገኝበት ስፍራ ነው ትላለች፡፡

’’ለእኔ ያልተገደበ ድጋፍ አላቸው፡፡ በእያንዳንዱ እርምጃዬ ከጎኔ ነበሩ፤ ያለእነርሱ ድጋፍ እዚህ ደረጃ አልደርስም ነበር፡፡’’ ስትል የትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሚና ትገልፃለች፡፡ በሦስት ዓመት የሚበልጣት ወንድም ያላት ናኦሚ ለኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ የተለየ ፍቅር አላት፡፡ ቤተሰቦቿም የትውልድ ሃገራቸውን ባህል እና እሴት እንድታውቅ አድርገው እንዳሳደጓት ትናገራለች፡፡ ካደገችበት ማህበረሰብ አልፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነችው ናኦሚ ግርማ አሁንም ድረስ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ አልተለያትም፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review