ረጅም ዓመታትን የተሻገረ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉንም ዜጋ ያንሸራሸረ፣ የሚሊዮኖች እግር፣ ለከተማዋ ችግር መፍትሔ የሰጠ፣ የአባት አርበኞች ጅማሮ ከቢሾፍቱ እስከ ትሬንታ ኳትሮ አውቶቡስ አገልግሎት…..::
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር 1935 የጣሊን ወረራ በአባቶች መራራ ተጋድሎ ሲያከትም፣ የግራዚያኒ ጦር ይጠቀምባቸው የነበሩ ትሬንታ ኳትሮ የተሰኙ 10 አውቶቡሶች በአዲስ አበባ ከተማ ተገኙ። በኢትዮጵያ ከድል ማግስት፣ አዲስ ዘመን ሲነጋ አዲስ ብርሃን ሲፈካ የጠላት ወንበር በአርበኞች ሲተካ ከተጀመሩት ዘመናዊ አገልግሎቶች አንዱ የአውቶቡስ አገልግሎት ነው። የአዲስ አበባ ከተማ የአውቶቡስ አገልግሎት በአራት የስምሪት አቅጣጫዎች በ15 ሳንቲም ክፍያ በአስር አገልግሎት ሰጭ አውቶቡሶች አሀዱ ተብሎ ተጀመረ።

አቀበት ቁልቁለቱን፣ ወጣት አዛውንቱን፣ ድሃ ሳይለይ ሀብታም፣ እናትና ልጅን፣ ሩቅና ቅርቡን፣ ሌሊት በቁር ቀን በሀሩር፣ እየሰራ ዛሬ ላይ የደረሰው የአዲስ አበባ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዘመን ተሻጋሪና አነጋጋሪ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል። ድርጅቱ፣ በአዲስ ሪፎርም ራሱን በማደራጀት በመንግሥት መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ 74/2014 መሰረት ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርትንና የአዲስ አበባ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅትን በማዋሀድ፣ የአዲስ አበባ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በሚል ስያሜ በ190 የጉዞ መስመሮች፣ በ5 ቅርጫፍ ጣቢያዎች እና 1ሺ 230 አውቶቡሶች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ድርጅቱ አሁን ላይ ከሪፎም በፊት የነበሩ ኋላቀረ አስራሮችን ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማሸጋገር፣ የተግባርና የአመለካከት ማስተካከያ በማድረግ በተሟላ አሰራር በዘመናዊ መንገድ ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ ይገኛል። የአዲስ አበባ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አካሉ አሰፋ እንዳሉት፣ የአውቶቡስ ስምሪት መስመር መከታትያ፣ የቲኬት አሰራርን፣ የመቆሚያ ሰዓት፣ የነዳጅ ፍጆታን፣ የጋራዥና እጥበት ስፍራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስተሳስርና በመከታተል ዘመናዊ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

አቶ አካሉ አክለውም፣ የቴክኒክ ምርመራ ዘርፉን ዘመናዊና ፈጣን በማድረግ፣ ከብልሽት በመታደግ እና ፈጥኖ ወደ አገልግሎት ከመመለስ አንጻር በትኩረት በመሰራቱ በዘጠኝ ወራት ብቻ እስከ 10 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል። የድርጅቱ የቴክኒክና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምሩ ፉፋ በበኩላቸው፣ ከመደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የገቢ አቅምን ለማሳደግ የሚያግዙ የአሽከርካሪዎች ስልጠና፣ የተማሪዎች ሰርቪስ፣ የነዳጅ አጠቃቀም ልኬት፣ የክሬን አገልግሎትና የማስታወቂያ ስራዎችን እንዲሁም የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
የ82 አመታት የካበተ ልምድ፣ ከዘመን ጋር ሲሞረድ፣ የተቋሙ ከፍታና ደረጃ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎቱ የደረጀ መሆኑን የተቋሙ አሰራር ያረጋግጣል።
በአለኸኝ አዘነ