የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ 70ኛ ዓመቱን አከበረ

You are currently viewing የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ 70ኛ ዓመቱን አከበረ

AMN – ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም

የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ በትናንትናው እለት 70ኛ ዓመቱን አክብሯል፡፡

የክብረወሰን መዝጋቢው ድርጅት በዚሁ እለት ባለፉት 70 ዓመታት ያልተመዘገቡ 70 አዳዲስ ሪከርዶችን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ በለንደን ከተማ በፈረንጆቹ 1955 ነሀሴ 27 ላይ ነበር የመጀመሪያውን የድንቃ ድንቅ መፅሀፍ ያሳተመው።

እንግዳ ክስተቶችን የሚመዘግበው መፅሀፍ በወቅቱ ምን ይዞ እንደመጣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የማወቅ ጉጉት ፈጥሯል። ሀሳቡ የተጠነሰሰው በወቅቱ የጊነስ ቢራ ፋብሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ከነበሩት ከሰር ህዩ ቢቨር ሲሆን፣ መልስ ባይገኝለትም በአውሮፓ ፈጣን የወፍ ዝርያ የትኛው ነው የሚለው አከራካሪ ጉዳይ የድንቃ ድንቅ መዝገብ በሚል ለተሰየመው መፅሀፍ ጥንስስ ሆኗል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በስፖርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በአስደናቂ የሰው አካል እና በልዩ ክህሎት የተመዘገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ክብረወሰኖች በዓመታዊው መጽሐፍ ታትመዋል። በዓለም ዙሪያም 155 ሚሊዮን ቅጂዎች ተሽጠዋል። ትላንት ረቡዕ 70 ዓመት የደፈነው ጊነስ ወርልድ ሬከርድስ እስካሁን ያልተመዘገቡ 70 አዳዲስ ሪከርዶችን ይፋ አድርጓል።

ከነዚህም መካከል ፈጣን የ400 ሜትር የጆንያ ሩጫ ውድድር እና ወደ ኤቨረስት ተራራ በብስክሌት ለመውጣት በጣም ፈጣኑ ጊዜ ተጠቃሽ ናቸው። የምስረታ በዓሉን አስመልክቶም የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ዋና አዘጋጅ ክሬግ በነዚህ ዓመታት በዓለም ዙሪያ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የጥንካሬ፣ የክህሎት እና የጽናት ብቃቶችን አይተናል እናም ይቀጥል ሲል ተናግሯል።

አሁንም አዳዲስ ነገር በጉጉት እየጠበቅን፣ የአሁኑን እና ቀጣዩን ክብረወሰን ሰባሪ ትውልድ እያከበርን እንገኛለን ማለቱን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review