የአፍሪካ ህብረት ሴቶች በአህጉራዊ የሰላም ግንባታ እና መረጋጋት ያላቸውን ሚና የበለጠ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አዲስ ከተሾሙት የህብረቱ የሴቶች፣ የሰላም እና ደህንነት ልዩ ልዑክ አምባሳደር ላይቤራታ ሙላሙላ ጋር በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ስትራቴጂካዊ ውይይት አድርገዋል።
ሊቀ መንበሩ በአፍሪካ ህብረት የግጭት አፈታት ጥረቶች ውስጥ የሴቶች መሪነት እና ደህንነት ጥበቃ ዋንኛ የትኩረት ማዕከል መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።
በተለይም ሴቶች ግጭት እና ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ጉዳዩ የተለየ ትኩረት እንደሚያሻው ገልጸዋል።
የአምባሳደር ላይቤራታ የስራ ኃላፊነት እንደ አጀንዳ 2036 እና የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት መዋቅር (APSA) ካሉ የረጅም ጊዜ ግቦች ጋር ከመተሳሰሩ ባሻገር ህብረቱ የሚመራቸውን ድርድሮችና የሰላም ሂደቶች ላይ ከሴት አሸማጋዮችና የስርዓተ ጾታ እይታዎች ጋር የማቆራኘት ግብ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ከንግግር ባለፈ ለሴቶች ጥበቃ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገር በቀል ሲቪክ ማህበራት በሴቶች ጉዳይ ጠንካራ ትብብር መፍጠርና አህጉራዊ የተጠያቂነት ስርዓትን የበለጠ ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
በሴቶች ለሚመሩ ኢኒሼቲቮች ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር ይገባል ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ በዚህ ረገድ አፍሪካ ህብረት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ሙሉ ድጋፉን እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።
ውይይቱ የአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ እና የአባል ሀገራትን ቃል ኪዳኖች ወደሚጨበጥ ውጤት በመቀየር ሴቶችና ልጃ ገረዶች በአህጉሪቷ የሰላምና ደህንነት ሂደቶች ያላቸውን ሚና በማሳደግ ለውጥ ለማምጣት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ መግለጹን ከህብረቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።