ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ወደ ምግብ ዋስትና እና የግብርና ሽግግር በምናደርገው ጉዞ አንድ ሌላ እጥፋት ላይ በመድረሳችን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንኳን ደስ አለን ብለዋል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት መፈረሙን ገልፀዋል።
2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ይኽ ሜጋ ፕሮጀክት በአመት እስከ ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የሚያመርት ሲሆን ይኽም ኢትዮጵያን ከአለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ ያደርጋታል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በሀገር ውስጥ የሥራ እድል ይፈጥራል፤ ለዘመናት ለተፈተኑት ገበሬዎቻችን አስተማማኝ የማዳበሪያ አቅርቦት ያረጋግጣል፤ ለምግብ ሉዓላዊነት መንገዳችንም ወሳኝ ርምጃ መውሰዳችንን ያመላክታልም ብለዋል።
በመላው አኅጉሩ ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት በማጠናከር ሕዝባችንን እና ነጋችንን የሚጠቅሙ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን የመከወን ጽኑ አቋማችንን ያሳያልም ብለዋ።
የዛሬውን የፊርማ ስምምነት ተከትሎ ፋብሪካው በሚቆምበት ስፍራ ፕሮጀክቱን በይፋ እንደሚያስጀምሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኽን ታሪካዊ ጉዞ ጀምረናል። ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን በማለት ገልፀዋል።