የቤርሙዳ ትሪያንግልን ሚስጥር ፈትቻለሁ ያሉት ተመራማሪ

You are currently viewing የቤርሙዳ ትሪያንግልን ሚስጥር ፈትቻለሁ ያሉት ተመራማሪ

AMN – ነሐሴ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

በፖርቶሪኮ እና በፍሎሪዳ መካከል የሚገኘው ቤርሙዳ ትሪያንግል በመባል የሚታወቀው የውሀ አካል የአፈ ታሪክ እና የሚስጥራዊ እንቅስቃሴ መገኛ ስለመሆኑ ለ500 አመታት ሲነገርለት ቆይቷል።

በዚህ አካባቢ አውሮፕላኖች በበረራ ላይ እያሉ ለመግለጽ በሚያስቸግር ሁኔታ ደብዛቸው ጠፍቷል፤ መርከቦች ስብርባሪያቸው እንኳን ሳይገኝ ሰምጠዋል።

700 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ለመቶ አመታት እንቆቅልሸ ሆኖ የሰነበተው ስፍራ በከፍተኛ ደረጃ ለሴራ ትንታኔ የተጋለጠ እንደሆነ ይነገርለታል።

አንዳንዶች ስፍራው ከዚህ አለም ያልሆኑ ፍጥረታት (ኤሊያን) ምርምር ለማድረግ ሰዎችን ሰውረው የሚወስዱበት ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ከፍተኛ ሀይል ያለው አካል በጥልቁ ባህር እንደሚኖር በተለያዩ መንገዶች ሀሳባቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል።

ተመራማሪዎች የዚህን ስፍራ ጥልቅ ሚስጥር ለማወቅ ዘመናትን የፈጀ ጥናት እና ምርምር ቢያደርጉም ብዙሀኑን ሊያስማማ የሚችል ፍሬያማ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ አልቻሉም።

ከሰሞኑ የቤርሙዳን ሚስጥር ፈትቻለሁ ያሉት የሳውዝሀምፕተን ዩኒቨርስቲ ኦሺኖግራፊ ባለሙያ ዶክተር ሳይመን ቦክሳል፤ በቤርሙዳ ትሪያንግል አካባቢ ለተከሰቱ ተደጋጋሚ መሰወሮች ምክንያቱ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ማዕበል እንደሆነ ተናግረዋል።

ተመራማሪው 165 ሜትር የምትረዝመው የአሜሪካ ባህር ሀይል ንብረት የሆነችው እና 306 አባላትን ይዛ እ.ኤ.አ በ1918 ወደ ብራዚል ስትጓዝ ደብዛዋ የጠፋውን መርከብ ለአብነት ጠቅሰዋል።

ዴይሊ ሜይል ይዞት በወጣው ዘገባ ይቺ መርከብ 30 ሜትር ቁመት ባለው ማዕበል እንደተመታች እና ደብዛዋ እንደጠፋ ተመራማሪው መናገራቸውን ዘግቧል።

ተመራማሪው አክለውም ይህ ከፍተኛ ቁመት እና ሀይል ያለው ማዕበል የአካባቢውን የአየር ጠባይ በፍጥነት በመቀያየር ቢያንስ 20 ለሚሆኑ አውሮፕላኖች መከስከስ ምክንያት ሳይሆን አንደማይቀርም የጥናታቸውን መላምት አስቀምጠዋል።

ባለፉት 100 አመታት በቤርሙዳ ትሪያንግል 50 መርከቦች እና ከ20 በላይ አውሮፕላኖች መጥፋታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሰዎች ከሳይንሳዊ ማብራሪያዎች ይልቅ የሴራ ትንታኔ ገለጻዎችን ማመን ይቀላቸዋል የሚሉት ዶክተር ሳይመን፤ ይህ ግኝቴ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንደማያገኝ አውቃለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review