የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) በአህጉሪቱ ስርጭቱ እያደገ የሚገኘውን የኮሌራ በሽታ ለመከላከል በመላ አህጉሪቱ የሚተገበር የድንገተኛ ጊዜ እቅድ ይፋ አድርጓል።
ተቋሙ የድንገተኛ ጊዜ ምላሽ እና መከላከል ሲል የጠራውን እቅድ ከአለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር እንደሚተገብር ነው ያስታወቀው።
ይህ እቅድ የበሽታውን የመለየት አቅም ማዳበር ፥ የምላሽ አቅምን ማሳደግ እንዲሁም የድንበር ተሻጋሪ ትብብርን ማጠናከር ላይ እንደሚያተኩር አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
በአፍሪካ በሚገኘው ደካማ የጤና ስርዓት እና በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ወረርሽኞች ምክንያት ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ነው ተብሏል።
እቅዱ ይፋ የሆነው በጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሱዳን የወረርሽኙ ከፍተኛ ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገች በምትገኝበት ወቅት ነው።
በሀገሪቱ በአንድ ሳምንት ብቻ 1200 አዳዲስ ተጠቂዎች እና 36 ሞት ተመዝግቧል፣ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ግንቦት ወር ጀምሮ ደግሞ የ158 ሰዎች ህይወት አልፏል።
በጦርነቱ ምክንያት የሀገሪቱ የጤና መሰረተ ልማቶች የደረሰባቸው ጉዳት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አዳጋች እንዳደረገው ነው የሚነገረው።
የአፍሪካ ሲዲሲ ባለስልጣናት መታከም እና መዳን የሚችለው የኮሌራ በሽታን ለመግታት የተቀናጀ ምላሽ ተግባራዊ ባለመሆኑ ስርጭቱ ከዚህም በላይ እንዳይስፋፋ ያሰጋል ብለዋል።
በዳዊት በሪሁን