የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና ቡድን በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የክረምት በጎ ፈቃድ የጤና ምርመራ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
ሆስፒታሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ከጀመረበት 2015 ዓ.ም ጀምሮ እሰከ አሁን ከ180 ሺህ በላይ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን በሆስፒታሉ የቤተሰብ ህክምናና የማህበረሰብ ጤና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ቢያድግልኝ አጥናፍ ተናግረዋል።
በቤት ውስጥ ህክምና ሳያገኙ ረጅም ጌዜያትን የቆዩ፣ መክፈል የማይችሉ ዜጎች፣ ስለ ጤና መረጃ የሌላቸው፣ በጊዜ መጣበብ ምክንያት ለጤና እክል ተጋላጭ የሆኑትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞችንም ተደራሽ በማድረግ ብቁና አምራች ዜጋ ለማፍራት አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በዘንድሮው መርሐ-ግብር ፣ተቋሙ በርካቶችን ተደራሽ በማድረግ በገንዘብ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የበጎ ፍቃድ ቡድኑ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የጥርስ፣ የቆዳ፣ የዓይንና የውስጥ ደዌ ህክምናን በነፃ መስጠቱን ዶክተር ቢያድግልኝ ተናግረዋል።
በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሠው ሀብት ስራ አመራርና ልማት ዳይሬክተር አቶ አስራት ገረመው በበኩላቸው የህክምና ቡድን በተቋሙ ለሚገኙ 500 የሚጠጉ ሰራተኞች አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረው፤ ይህም ቅድመ በሽታን ለመከላከልን ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
አቶ አስራት አክለውም የተሠጠው አገልግሎት ባለሙያዎቹ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ የሚያጠፉትን ጊዜ እና ከፍተኛ ወጪ መቆጠብ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
የአለርት ሆስፒታል በተቋሙ በመገኘት ላበረከተው አስተዋፅዖ ምስጋና ያቀረቡት ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይም የተቋሙ ሠራተኞች ጤናማና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ከሆስፒታሉ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
በሚካኤል ህሩይ