ድፍረት በተሞላበት አጨዋወቱ እና በረጅም ፀጉሩ የሚታወሰው ግብ ጠባቂ ፡- ሬኔ ሂጉይታ

You are currently viewing ድፍረት በተሞላበት አጨዋወቱ እና በረጅም ፀጉሩ የሚታወሰው ግብ ጠባቂ ፡- ሬኔ ሂጉይታ

AMN – ነሃሴ 23/2017 ዓ.ም

በእግር ኳስ የግብ ጠባቂዎች ትልቁ ሃላፊነት ግብ እንዳይቆጠር ሙከራዎችን ማምከን ነው፡፡ አሁን ላይ ሙከራ ማክሸፉ እንዳለ ሆኖ ይበልጥ በጨዋታው እንዲሳተፉ ይበረታታሉ፡፡

በቀደመው ጊዜ ግን ይህን ማሰብ ይከብዳል። ነገር ግን በዘመኑ አንድ የተለየ ግብ ጠባቂ ነበር። ኮሎምቢያዊው ሬኔ ሂጉይታ። የ”ስዊፐር ጎል ኪፐር” ማለትም ከግብ ክልሉ ወጥቶ መጫወት የመቻል ሚናን ያስጀመረ ተደርጎ ይቆጠራል።

ድፍረት በተሞላበት አጨዋወቱ ፣ በረጅም ፀጉሩ እንዲሁም ለየት ባለ ባህሪው የሚታወቀው ሬኔ ሂጉይታ ለበርካታ ግብጠባቂዎች አርአያ መሆን የቻለ ነው።

” ኤል ሎኮ” ስፓኒሽ ተናጋሪዎች የአእምሮውን ጤንነት ለሚጠራጠሩት ሰው የሚሰጡት ስያሜ ነው። በእኛ ወፈፌው ልንለው እንችላለን። ወፈፌው ለኮሎምቢያዊው የምንግዜም ምርጥ ግብ ጠባቂ ሬኔ ሂጉይታ የተሰጠ ቅፅል ስም ነው።

በሜዳ ላይ በሚፈፅማቸው ለማመን የሚከብዱ ስራዎቹ ያገኘው ቅፅል ስሙ እንደሆነ ይነገራል። ድፍረቱ በተለይ ለእርሱ ቡድን ደጋፊዎች አጥወልውሎ ይጥላል።

ልክ እንደተዋጣለት የመስመር አጥቂ ኳስ እየገፈ ተጫዋቾችን ለማለፍ ይሞክራል። የግብ ክልሉን በብዙ ሜትር ርቆ ወጥቶ ተጫዋች ለማለፍ ሲሞክር መመልከት ለደጋፊ ምቾት የሚሰጥ አይደለም። እርሱ ግን ግድ የለውም።

ማንነቱን አይተው አሰልጣኞችም ደፍረው አይገስፁትም። የቡድን አጋሮቹም ወደ ግብ ተመለስ የማለት ድፍረት የላቸውም። ጭራሽ አንድ ሁለት እየተቀባበሉ መጫወቱን እንዲገፋበት ያበረታቱታል።

ምዕራብ ጀርመን በድል ያጠናቀቀችበት የ1990 የጣልያን አለም ዋንጫ በተለየ ሁኔታ የሚታወሰው በሬኒ ሂጉይታ ነው። ግብ ጠባቂዎች የገዛ የቡድን አጋራቸው የሚሰጣቸውን ኳስ በእጅ መያዝ ህጉ ይፈቅድላቸው ስለነበር እርቀው መውጣት አይፈልጉም።

ሬኔ ሂጉይታ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ሲጫወት ያዩ ተመልካቾች በግርምት አዩት። በርካቶችን ሲያዝናና የቆየው ግብጠባቂ ድፍረት የተሞላበት አጨዋወቱ ግን ጉድ ሰርቶታል።

በጥሎ ማለፍ ዙር ኮሎምቢያ ከ ካሜሩን ሲጫወቱ የካሜሩኑን አጥቂ ሮጀር ሚላ አታልዬ አልፋለው ሲል ተቀምቶ ግብ ተቆጠረበት። በእርሱ ስህተት ሃገሩ ዋጋ ከፈለች። በዚህ ትልቅ መድረክ ላይ የሰራው ስህተት ግን በፍፁም አጨዋወቱን አላስቀየረውም።

እኤአ መስከረም ስድስት 1995 እንግሊዝ ከ ኮሎምቢያ በዌምብሌይ ስታዲየም የወዳጅነት ጨዋታ ሲያደርጉ የእንግሊዙ አማካይ ጂሚ ሬድናፕ ለማሻማት አጥብቆ የመታው ኳስ አቅጣጫ ስቶ እየተምዘገዘገ ወደ ኮሎምቢያ ግብ ያቀናል።

ሬኔ ሂጉይታ በቀላሉ በእጁ መያዝ እየቻለ እንደ አሞራ ተንሳፎ ሁለት እግሮቹን ከጭቅላቱ በላይ አንስቶ በማጠፍ ኳሱን በተረከዙ መለሰ።

ተመልካቾች ጤንነቱን ተጠራጠሩ። እርሱ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥሮ ጨዋታውን ቀጠለ። ከጨዋታው በኋላ ስለ ሁኔታው ሲጠየቅ “ለዓመታት ስለማመድ ነበር” ብሎ ጀነን ብሎ መልስ ሰጠ።

በሀገሩ ኮሎምቢያ ፣ ቬንዙኤላ እንዲሁም በአውሮፓ ለስፔኑ ሪያል ቫያዶሊድ ተጫውቶ ያሳለፈው ሬኔ ሂጉይታ ለብሔራዊ ቡድኑ 68 ጊዜ ተጫውቷል።

ሬኔ ሂጉይታ ከግብ ክልሉ ወጣ እያለ ኳስን ቀለል አድርጎ በመጫወት ብቻ ሳይሆን ግብ በማስቆጠርም ስሙ የሚነሳ ግብጠባቂ ነበር።

የራስመተማመን ችግር የሌለበት ሂጉይታ 35 ግብ ከፍፁም ቅጣት ምት ፣ ሰባት ከቅጣት ምት ፣ አንድ ደግሞ ከግብ ክልሉ አካባቢ አሮቆ በመምታት አጠቃላይ 43 ግቦችን አስቆጥሯል።

ይህም በርካታ ግብ ካስቆጠሩ ግብጠባቂዎች መሀል አምስተኛ ደረጃ ያስቀምጠዋል። ከዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ጋር የቅርብ ጋደኛ የነበረው ሂጉይታ የትውልድ ከተማው ሜዴሊን ክለብ በሆነው አትሌቲኮ ናሲዮናል የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆኖ እየሰራ ይገኛል።

ከሁለት ቀን በፊት 59 ዓመቱን የያዘው ሂጉይታ ከእነ ብዙ ትዝታዎቹ ህይወትን እየገፋ የሚገኘው በዚህ መልኩ ነው።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review