ኢትዮጵያ በ27ኛው የኢንተርፖል የአፍሪካ ቀጠና ዓመታዊ ኮንፍረንስ ላይ እየተሳተፈች ነው

You are currently viewing ኢትዮጵያ በ27ኛው የኢንተርፖል የአፍሪካ ቀጠና ዓመታዊ ኮንፍረንስ ላይ እየተሳተፈች ነው

AMN ነሐሴ 23 ቀን 2017

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዑካን ቡድን በደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕታውን ከተማ ከነሃሴ 21 እስከ 23 ቀን 2017 ዓ.ም እየተካሄደ በሚገኘው 27ኛው የኢንተርፖል የአፍሪካ ቀጠና ዓመታዊ ኮንፍረንስ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

በኮንፈረንሱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የፖሊስ ኃላፊዎች፣ የኢንተርፖል አመራሮች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከፖሊስ ጋር በአጋርነት የሚሰሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት ፕሮፌሰር ካቻልያ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ተቀዳሚ ሚኒስትር ሲሆኑ የድርጅቱ አባል ሀገራት ለአፍሪካ እና ለዓለም ሰላም መስፈን በትብብር በመስራት እያደረጉ ያሉትን ጥረት አድንቀው ሀገራቸው ደቡብ አፍሪካ ከአባል ሀገራት ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

በኮንፍረንሱም የድንበር ደህንነትን ማጠናከር፣ ፈጣን የመረጃ ልውውጥን በማሳደግ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የሚደግፉትን ለመቆጣጠር ተቋማዊ አቅምን ለማሻሻል፣ የፖሊስ የመረጃ ልውውጥ ማጠናክር እና የመረጃ ቋት ተደራሽነት ማስፋት እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን በጋራ ወንጀል መከላከል ሥራ አፈፃጸም፣ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት፣ በቀጣይ ለማከናወን ስለታቀዱ ተግባራት እና የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት እየተደረገባቸው ልዩ ልዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሸነር ጀነራል ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን ከኢንተርፖል ፕሬዝዳንት ሜጀር ጀነራል ዶ/ር አህመድ ናስር አል ራይሲ እና ዋና ፀሀፊ ቫልዴሲ ኡርኪዛ ጋር ከአፍሪፖል፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ብራዚል፣ ከእንግሊዙ ናሽናል ክራይም ኤጀንሲ ሃላፊዎች እና ከተለያዩ ሀገራት የፖሊስ ኃላፊዎች እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸዉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡

በውይይቱም የኢትዮጵያ ፖሊስ ከድርጅቱና አባል ሀገራት ጋር በቅርበት በመስራት የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይ በሽብርተኝነትን ፋይናንሺያል፣ የሳይበር፣ ኬሚካልና ራዲዮሎጂካል ወንጀሎችንና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የተቀናጀ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ትብብር የበለጠ እንዲጠናከር አሳስበው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንጅሎችን በጋራ ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሸነር ጀነራል ኢትዮጵያ በቀጣይ በ2027 የሚደረገውን የኢንተርፖል አፍሪካ ሪጅናል ኮንፍረንስ ዓመታዊ ጉባዔ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርበው እና ከሚመለከታቸው የኢንተርፖል ኃላፊዎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ኢትዮጵያ እንደምታዘጋጅ ውሳኔ ተላልፉዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review