አሜሪካ የቀድሞ የብራዚል ፕሬዝዳንት ጉዳይን እየዳኙ በሚገኙ ዳኛ ላይ ማዕቀብ ጣለች

You are currently viewing አሜሪካ የቀድሞ የብራዚል ፕሬዝዳንት ጉዳይን እየዳኙ በሚገኙ ዳኛ ላይ ማዕቀብ ጣለች

AMN – ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም

የአሜሪካ ግምጃ ቤት የቀድሞ የብራዚል ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮን ጉዳይ እየተከታተሉ በሚገኙት ዳኛ ላይ ማዕቅብ ጥሏል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት በ2022 በተደረገው ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ስልጣን ላለመልቀቅ እና መፈንቅለ መንግስት ለመፈጸም አሲረዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ በቤት ውስጥ እስር ላይ ናቸው።

የፍርድ ሂደቱን እየዳኙ የሚገኙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አሌክሳንደር ዲ ሞሪስ፤ ቦልሶናሮ ጉዳያቸው ፍርድ እስኪያገኝ ድረስ ከሀገር እንዳይወጡ እና በቤታቸው አቅራቢያም ፖሊስ እንዲሰማራ አዘዋል።

ዳኛው በነጻነት የመናገር መብት ገድበዋል እንዲሁም ከህግ አግባብ ውጭ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የመንቀሳቀስ መብት ተጥሷል ያለው የአሜሪካ መንግስት ማዕቀብ ጥሏል።

አሁናዊው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ውሳኔ በሀገሪቱ የፍትህ ስርአት ላይ ጣልቃ መግባት ነው ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሀላፊ ስኮት ቤሴንት፤ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ከህግ አግባብ ውጭ ፖለቲካዊ ውሳኔ አስተላልፈዋል እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት ተባባሪ ሆነዋል ሲሉ ከሰዋል።

በማዕቀቡ መሰረትም ዳኛው በአሜሪካ ያሏቸውን ማናቸውንም ንብረቶች እንዳያንቀሳቅሱ ታግደዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወዳጅ የሆኑት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሐምሌ ወር የ50 በመቶ ታሪፍ በብራዚል ላይ ለመጣል ወስነው ነበር።

ሆኖም ከቆይታ በኋላ ከአቋማቸው በመለሳለስ የብራዚል ቁልፍ ዘርፎች የሚባሉ የሃይል ፣ የብርቱካን ምርት እና የአውሮፕላን መገጣጠሚያዎች ከማዕቀቡ ውጪ እንዲሆኑ አድርገዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review