በጫካ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች የሰላም አማራጭ የተቀበሉትን የቀድሞ ታጣቂዎች ፈለግ ሊከተሉ እንደሚገባ የኮማንዶና የአየር ወለድ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል አዛዥና የሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አበባው ሰይድ አስታወቁ።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የቀድሞ ታጣቂዎችን በደብረ ብርሀን ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል በተሀድሶ ስልጠና መልሶ የማቋቋም ስልጠና መሰጠት ጀምሯል። በሥነ-ስርዓቱም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የኮማንዶና የአየር ወለድ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል አዛዥና የሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አበባው ሰይድ፤ ጽንፈኛ ኃይሎች በፈጠሩት የጸጥታ ችግር የክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አስተናግዷል ብለዋል። በዚህ መነሻነትም የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት መወጣቱን ጠቁመው፤ በክልሉ ህዝብ ላይ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር መቀልበስ ያስቻሉ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
አሁንም የሀገር ውስጥና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን ተልዕኮ በማንገብ የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ አስተማሪ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ከተሳሳተ አካሄድ መመለሳቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ተናግረዋል። በጫካ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች የሰላም አማራጭ የተቀበሉትን የቀድሞ ታጣቂዎች ፈለግ ሊከተሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በቀጣይም የተሃድሶ ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ማህበረሰባቸው ሲመለሱም ቀሪዎቹ በጫካ ያሉ የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉና የሰላምና የልማት አካል እንዲሆኑ መስራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል። የመከላከያ ሠራዊት ተወካይና የብሔራዊ ተሃድሶ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ፤ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሃድሶ ስልጠና አልፈው ሰላማዊ ህይወት እንዲኖሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በተሃድሶ ስልጠና የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎችም የስነ-ምግባርና የሥነ-ልቦና ግንባታ ትምህርት በመከታተል የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ሰላማዊ ህይወት እንዲኖሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የጽንፈኝነት አካሄድ ሀገርና ህዝብን ይጎዳል ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ፤ በጫካ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል መደበኛ ሕይወታቸውን መምራት እንደሚኖርባቸው ጥሪ አቅርበዋል። የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቴ የሱፍ (ዶ/ር)፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተወሰደ ህግ የማስከበር እርምጃ ጽንፈኛ ኃይሎችን ከህዝብ የመነጠል ስኬታማ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታጣቂ ኃይል የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በተሃድሶ ስልጠና አልፎ መደበኛ ህይወቱን የሚመራበት ዕድል መፍጠር እንደተቻለ አስረድተዋል። የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ጽንፈኛው ሃይል ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር እንደሚሰራ የተገነዘቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በደብረ ብርሀን ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል ሰልጣኝ የሆኑት የቀድሞ ታጣቂዎች ተወካይ ሻምበል ግርማ ዘነበ፤ ትክክለኛ ትግል መስሎን ለሁለት ዓመታት ያህል ህዝባችንን ስንበድል ቆይተናል ማለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአማራ ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው በተሳሳተ የትጥቅ ትግል ሳይሆን በሰለጠነ ሰላማዊ የምክክር አውድ መሆኑን በመገንዘብ የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ህዝባቸውን ለመካስ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።