የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኛቸው የነበሩት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ጠባቂዎች እንዲነሱ ወስነዋል።
በሀገሪቱ ህግ መሰረት የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ከቢሮ ከወጡ በኋላ ለ6 ወር ያህል የደህንነት መስሪያቤቱ (ሴክሬት ሰርቪስ) ጥበቃን የማግኘት መብት አላቸው። ይህ የጥበቃ ጊዜ ባሳለፍነው ሰኔ የሚጠናቀቅ ቢሆንም የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ካማላ ሃሪስ ለአንድ ዓመት ያህል እርሳቸው እና ቤተሰባቸው እንዲሁም ንብረቶቻቸው በሴክሬት ሰርቪስ እንዲጠበቅ ጊዜውን አራዝመውላቸው ነበር።
ትራምፕ ጥበቃው እንዲነሳ ያዘዙት ሃሪስ “107 ቀናት” በሚል የ2024 ያልተሳካ የምርጫ ቅስቀሳቸውን የሚያሳይ መጽሀፋቸውን ለማስተዋወቅ በመላው አሜሪካ ለመጓዝ አንድ ሳምንት ሲቀራቸው ነው። ይህን ተከትሎ ካማላ ሃሪስን የሚጠብቁ የደህንነት አባላት ከመስከረም 1 ጀምሮ ስራቸውን እንዲያቋርጡ ታዘዋል። በቀጣይ የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዚዳንት የደህንነት ጉዳይ ምን ምላሽ እንደሚያገኝ ባይታወቅም፣ የካሊፎርኒያ እና ሎስአንጀለስ ግዛት አስተዳዳሪዎች ጉዳዩን በመቃወም መግለጫ አውጥተዋል።
ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ልጆች ሀንተር እና አሽሊ ባይደን እንዲሁም የብሔራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች የቀድሞ ዳይሬክተር አንቶኒ ፋውቺን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎችን የደህንነት ጥበቃ አባላት እንዲነሱ አድርገዋል። እነዚህ ሰዎች በሴክሬት ሰርቪስ ሲደረግላቸው የነበረውን ጥበቃ በግል የጥበቃ ድርጅቶች ለማስደረግ ቢያስቡ በዓመት እስከ 1 ሚሊየን ዶላር ወጪ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ቢቢሲ ዘግቧል።
በዳዊት በሪሁን