በአፍሪካ ትስስር እንዲጠናከር የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing በአፍሪካ ትስስር እንዲጠናከር የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

AMN – ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስር የበለጠ እንዲጠናከር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ይበልጥ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

“ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ለአፍሪካ ውህደት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 15ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኮሙኒኬሽን ማህበር ጉባኤ ተጠናቋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተካሄደው ይህ ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ መሆኑም ተገልጿል።

የጉባኤው አስተባባሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህርት አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር)፣ በአፍሪካ ትስስር እንዲጠናከር የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል። በአፍሪካ ጉዳይ አንድ ዓይነት ዕይታ እንዲኖር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአህጉሪቷ ትስስር እንዲጠናከር አንድ ቦታ ያለው መልካም ተሞክሮ ለሌላው እንዲደርስ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የተበታተነ አቅምን አንድ ላይ በማምጣት የአህጉሪቷን እድገት ማሳለጥ እንደሚገባ ገለጸው፣ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ግኝቶችን ለህዝቡ በማቅረብ ተጨባጭ ስራዎችን ማሳወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል። የማህበሩ አባል ካረን አጎላ (ፕ/ር) በበኩላቸው፣ የአፍሪካ መገናኛ ብዙሃን የአህጉሪቷን እድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን በትኩረት ማከናወን አለባቸው ብለዋል።

አህጉራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። ጁሊየት ማሻሪያ (ፕ/ር)፣ አፍሪካን በጋራ ለመቀየር የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ነው ያሉት። የአፍሪካ ሀገሮች የጋራ እጣ ፈንታ ስላላቸው በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በጥናትና ምርምር በመታገዝ ለአህጉሪቷ ልማት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዊኒስተን ማኖ (ፕ/ር) በበኩላቸው፣ ሀሰተኛ መረጃን በመከላከል አፍሪካን የሚገልፁ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝቡ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል። የአፍሪካን መልካም ገጽታ የሚያሳዩ ዘገባዎችን በማቅረብ ትብብርንና ወንድማማችነትን ማስረጽ እንዲሁም የልማት ስራዎችን በማጉላት አብሮነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የኮሙኒኬሽን ማህበር ፕሬዚዳንት ማርጋሬት ጁኮ (ፕ/ር)፣ የአፍሪካውያን ትስስር እንዲሳካ ሚዲያው ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የገለጹት።በአፍሪካ ሀገራት መካከል የባህል ልውውጥ በማድረግ መልካም ተሞክሮዎች ጎልተው እንዲወጡ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። ለአህጉሪቷ ጠቃሚ የሆኑ የጥናት ውጤቶችን በማሳተም ለህዝቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review