“ታሪካዊ ጉዞ ጀምረናል፤ ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር
እውቁ የዕፅዋት ሳይንስ ተመራማሪና ደራሲ ኤድዋርድ ሰለሞን ሃይምስ “አፈር እና ስልጣኔ” የተሰኘው ድንቅ የምርምር መፅሐፍ እ.ኤ.አ በ1952 አሳትመዋል። በመጽሐፉ በግልፅ እንደሰፈረው ጀርመናዊው ሳይንቲስት ፍሪትዝ ሀበር እ.ኤ.አ በ1909 ለመጀመሪያ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያን ቀመመ፡፡
ይህ ግኝትም በግብርናው ዘርፍ የተሰማ ታላቅ ብስራት፤ የዓለምን ምርትና ምርታማነት ሂደት እስከ ወዲያኛው የቀየረ ግሩም መላ ሆነ፡፡ በእርግጥም ዜናው አፈር ጉርሱ፣ ልብሱና እስትንፋሱ ለሆነው የሰው ልጅ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ የአፈርን ምርታማነት ከፍ ለማድረግ ከእንስሳት ፍግ እስከ እፅዋት ቅሪተ አካል፤ ከአዕዋፍ ኩስ እስከ አፅም ብስባሽ ድረስ ብዙ ደክሟልና ይላሉ፣ እውቁ የዕፅዋት ሳይንስ ተመራማሪና ደራሲ ኤድዋርድ፡፡
በተለይ “ጉዋኖ” ይባል የነበረው የአዕዋፍ ኩስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የምድራችን ውዱ ሸቀጥ ነበር፡፡ አንድ ፖውንድም ያህል መጠን ያለው ጉዋኖ እስከ 76 ዶላር ይሸጥ እንደነበር “አፈር እና ስልጣኔ” በተሰኘ መፅሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡ አንዳንድ ሀገራትም ጉዋኖን ለማግኘት ጦር እስከ መማዘዝ ይደርሱ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ እናም በጀርመናዊው ሳይንቲስት ድንቅ ምርምር የተገኘው ማዳበሪያ በዓለም የስልጣኔ ምዕራፍ ላይ ድርሻው ከፍ ያለ ነው፡፡
የእፅዋት ሳይንስ ተመራማሪውና ባለ ብዙ ሙያዎች ባለቤት የሆኑት እና ከ60 በላይ የምርምር መፅሐፍትን ለዓለም ያበረከቱት ኤድዋርድ “አፈር እና ስልጣኔ” በተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት ዓለም በዘመናዊ መልኩ የተቀነባበረ ማዳበሪያን ካገኘች ወዲህ መልኳ ተለወጠ፡፡ ይህንን ማዳበሪያ በቀላሉ ያገኙ ሀገራትም ምርትና ምርታማነታቸውን የበለጠ ከፍ አደረጉ፡፡ አንዳንዶቹም በምግብ እህል እራሳቸውን ቻሉ፡፡
ይህንን ማገኘት ያልቻሉ ሀገራት ደግሞ ለከፋ ችግር መጋለጣቸው አይቀሬ ሆነ፡፡ ለአብነትም በሂደት ታሪኩ የተቀየረ ቢሆንም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ብዙ አውሮፓውያን ወደ አሜሪካ የመሰደዳቸው ምስጢርም ይህ ነበር። ምርትና ምርታማነትን ከፍ የማድረግ በተለይም በምግብ እህል እራስን የመቻል ጉዳይን ወደ አፍሪካ ስናስጠጋው ምን ያህል አንገብጋቢ እንደሆነ ለመገመት እንደማያዳግትም የኤድዋርድ ሰለሞን ሃይምስ መፅሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡
በጀርመናዊው ቀማሚ የተገኘው የአፈር ማዳበሪያን በፋብሪካ የማቀነባበር ፈጠራ ዓለምን የነቀነቀና እ.ኤ.አ በ1918 የኖቤል ሽልማትንም ያስገኘ ነው፡፡ እስከ ዛሬም በዚህ መልኩ የተቀነባበረ ማዳበሪያን የማግኘት ጉዳይ ወይም ትልልቅ ፋብሪካዎችን የመገንባት ሂደት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ማርሽ ቀያሪ ነው፡፡
በመሆኑም የማዳበሪያ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ በስፋት ለተሰማሩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ማዳበሪያን በቀላሉ ማግኘት መቻል ማለት ፋይዳው ብዙ መሆኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ይንገስ አለሙ( ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
እንደ ይንገስ(ዶ/ር) ገለፃ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተሰሩ ሰፋፊ ስራዎችና መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት እየተመዘገቡ ያሉ አመርቂ ውጤቶች ያሉ ቢሆንም ዘርፉ ለሀገር እድገት ማበርከት ባለበት ልክ ጥቅም እየሰጠ አይደለም። ለዚህ ደግሞ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆኖ የማዳበሪያ ጉዳይ ለምርትና ምርታማነታችን ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡
ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ግብርና ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ እየሠራበት መሆኑን ያስታወሱት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ በዚህ ላይ ደግሞ የማዳበሪያ ፋብሪካው ሲጨመርበት ለውጡን ሙሉ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው ሐሙስ ደግሞ በኢትዮጵያ ስልጣኔ ላይ እምርታዊ ለውጥ የሚያመጣ አስደሳች ዜና ተሰምቷል፡፡ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካውን ለመገንባት ያደረጉት ስምምነት ነው፡፡
ስምምነቱን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክትም “ታሪካዊ ጉዞ ጀምረናል፤ ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን፡፡” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩልም “ከኢትዮጵያ ጋር ያደረግነው ስምምነት አፍሪካን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሻገር እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በጋራ ለያዝነው ራዕይ ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡” ሲሉ ዳንጎቴ መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ይንገስ አለሙ( ዶ/ር) እንደሚሉት የማዳበሪያ ፋብሪካው የሀገሪቱን ግብርና ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና በአስተማማኝ ማረጋገጥም ያስችላል፡፡
ከግብርና ሥራ ጋር ተያይዞ የማዳበሪያ ጉዳይ በአምራቹ በኩል ተደጋግሞ የሚነሳ ጥያቄ እንደሆነ ያስታወሱት ይንገስ (ዶ/ር) አሁን ስምምነት የተደረሰበት ግዙፉ የማዳበሪያ ፋብሪካ ሰፊ የስራ ዕድልን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከመፍጠር እና የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባሻገር ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና በምግብ እህል እራስን በማስቻል የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ ባለፈም ለአፍሪካውያን የሚተርፍ አበርክቶም ይኖረዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ አምርቶ በሚፈለገው ጊዜ እና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል። ለግብርና ምርት ዋና ግብዓት የሆነውን ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ አምርቶ የማቅረቡ ሥራ የዘርፉን ሽግግር የሚያፋጥን እንደሆነም አንስተዋል።
መንግሥት ማዳበሪያ ከውጭ ሀገራት ገዝቶ ለማስገባት በዓመት የሚያወጣው ወጪ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊየን ዶላር ደርሷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ መመረቱ የውጭ ምንዛሪን ለማዳን እንደሚያስችልም ጠቁመዋል። ፕሮጀክቱ ማዳበሪያ ለመግዛት በውጭ ሀገራት የሚያጋጥመውን ውጣ ዉረድ የሚያስቀር እና ከሀገር ሉአላዊነት ጋር የሚያያዝ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው እጅግ ዘመናዊ የሆነ የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ እና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች ስላሉት በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ያደርገዋል። ከሦስት ዓመት ብዙም ባልበለጠ ጊዜ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር በዓመት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚደርስ ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም አለው።
ፋብሪካው ለምርቱ ግብዓት በሶማሌ ክልል ውስጥ ከአንድ መቶ ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ በአቅራቢያው ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀም ሲሆን፣ ይህም በዓለም ላይ ካሉ በአንድ አካባቢ ምርታቸውን ከሚያቀናብሩ ግዙፍ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ነው ሲል ቢቢሲ መስክሮለታል፡፡
አብዛኞቹ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች የምርት ግብዓታቸውን ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመውሰድ የመጨረሻውን ምርት የሚያገኙ ናቸው። በዚህም የማጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎች ይጨምርባቸዋል። ፋብሪካው በሂደት የሚስፋፋ እና አዳዲስ ምርቶችን በማካተት የተለያዩ የማዳበሪያ ምርቶችን በማቅረብ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ውስጥ የማዳበሪያ ማምረቻ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሠራም ተገልጿል።
ከሦስት ዓመታት በኋላ ማዳበሪያ ፋብሪካው ሥራውን ሲጀምር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ማዳበሪያ ከሚያመርቱት ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ሞሮኮ፣ ግብፅ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ጋር የምትመደብ ትሆናለች።
በተጨማሪም አዲሱ ፋብሪካ ያለው የማምረት አቅም ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ እየተስፋፋ የሚሄድ በመሆኑ በአህጉሪቱ ካሉና በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሦስት ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ እንደሚሆንም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እና የዘርፉ ምሁራን በመመስከር ላይ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ወደ ምግብ ዋስትና እና የግብርና ሽግግር በምናደርገው ጉዞ አንድ ሌላ እጥፋት ላይ ደርሰናል ማለታቸውም ፋብሪካው እንደሀገር ሊኖረው የሚችለውን ወሳኝ ሚና ያመላክታል፡፡ በእርግጥም ይህ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ ከሕዳሴው ግድብ ቀጥሎ የዘመናት ጥያቄ የተመለሰበት፤ የሀገር ከፍታ በአስተማማኝ አለት ላይ የተመሰረተበት ታላቅ ስራ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁራን በመመስከር ላይ ናቸው፡፡
በመለሰ ተሰጋ