“መዲናችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪእንድትሆን የበለጠ መትጋታችንይቀጥላል”

You are currently viewing “መዲናችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪእንድትሆን የበለጠ መትጋታችንይቀጥላል”

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

ከተማዋ ፍጥነትን በማስተዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ  የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች

አዲስ አበባ በርካታ ህዝብ የሚኖርባት፣ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑባት የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መናኸሪያ የሆነች ከተማ ናት። ድርብርብ ኃላፊነት የተሸከመችውን ከተማ እንደ ስሟ ውብና አዲስ፣ ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች የተመቸች ለማድረግ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በኮሪደር ልማት፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት፣ በፅዳትና አረንጓዴ ልማት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ተደራሽነትን በማሳደግ፣ ሰላምና ፀጥታዋን በማስጠበቅ እና በተለያዩ መስኮች የተሰሩ ስራዎች ውጤት እያመጡ፣ በዓለም አደባባይም በተለያዩ ጊዜያት እውቅና እና ሽልማት እያስገኙላት ይገኛል፡፡

ከትናንት በስቲያም አዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመሪያ በሆነውና “ብሉምበርግ ኢኒሺዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ” ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ባዘጋጀው ፍጥነትን ማስተዳደር ዓለም አቀፍ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡

ለሽልማት ከታጩ ከተሞች አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ መሆኗን ነው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የገለፀው፡፡ በኢንሼቲቩ ውስጥ ያሉ ከተሞችና አስተዳደሮች ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በዓለም ጤና ድርጅት የሚመከሩ የፍጥነት ገደቦችን ወስደው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ አጠቃላይ የከተማ ውስጥ የፍጥነት ወሰን ስታንዳርድ በሰዓት ከ50 ኪሎ ሜትር በታች እንዲሁም በትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ገበያ ቦታዎችና ሌሎች ለትራፊክ ግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከ30 ኪሎ ሜትር ከሰዓት በታች በማድረግ በፍጥነት ማሽከርከርን መቀነስ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ስራ ላይ ማዋል ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ “ብሉምበርግ ፍላንተሮፒስ ኢንሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ባዘጋጀው የመንገድ ደህንነትን ማስተዳደር ላይ ከተማችን ባስመዘገበችው ተጨባጭ ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርቅ ሽልማት አሸናፊ በመሆኗ ታላቅ ክብር ተሰምቶናል፡፡ እውቅናው ከተማችን ፍጥነትን ለማስተዳደር እና የመንገድ ደህንነትን ለማሻሻል እየወሰደች ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ዳግም የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በሽልማቱ ያገኘነው 100 ሺህ ዶላር በቀጣይ የከተማዋ መንገዶች ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ጤናማ እና ለነዋሪው ተስማሚ፣ ምቹና አካታች እንዲሆኑ የሚያስችሉ የማሻሻያ ስራዎችን ለመስራት ተጨማሪ እገዛ ያደርጋል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በፍጥነት ማሽከርከር በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የ600 ሺህ ሰዎችን ህይወት ይቀጥፋል፡፡ ይኸውም በተለያየ ምክንያት ከሚሞተው የ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ህዝብ ግማሽ ያህል ማለት ነው፡፡ በፍጥነት ማሽከርከር በግጭት ወቅት ለከባድ የአካል ጉዳትና ሞት የሚያጋልጥ እንደሆነም የዓለም ጤና ድርጀት መረጃ ያሳያል፡፡

የብሉምበርግ ግብረ ሰናይ ድርጅት መስራች፤ የዓለም ጤና ድርጅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ጉዳቶች አምባሳደር እንዲሁም የኒው ዮርክ 108ኛው ከንቲባ የሆኑት ማይክል ብሉምበርግ እንደተናገሩት፣ በፍጥነት ማሽከርከር በዓለም ላይ በየዕለቱ 1 ሺህ 600 ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ይህ የትራፊክ አደጋ ልንከላከለው የምንችለው ዋነኛ የሞት እና ጉዳት መንስኤ ነው፡፡ 

አዲስ አበባ ፍጥነትን ለመቆጣጠር ምን ስራዎች እያከናወነች ነው?

በዓለም እና በሀገር አቀፍ ደረጃ አሳሳቢና ትኩረት ከሚሹ እና ለሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የትራፊክ አደጋ ተጠቃሽ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ በመዲናዋ የትራፊክ አደጋ የሚደርሰው በዋናነት በአሽከርካሪዎች ነው፡፡ ይህም ሲባል ትልቁ ስፍራ የሚይዘው በፍጥነት ማሽከርከር፣ የአደጋ መከላከያ ቆብ (ሄልሜት)፣ የደህንነት ቀበቶና ሌሎች የደህንነት እርምጃዎችን በአግባቡ አለመጠቀም፣ ጠጥቶ ማሽከርከር እና ሌሎች ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ 

በፍጥነት ምክንያት የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት እየተተገበረ ባለው የአምስት ዓመት ስትራቴጂ  የፍጥነት አስተዳደር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ፍጥነትን ለማስተዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የተሻሉ ተሞክሮዎችንና ስታንዳርዶችን በመውሰድና ከሀገራዊ ሁኔታ ጋር በማናበብ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ የሆነውን ሀገር አቀፍ የመንገድ ትራፊክ ደንብ ቁጥር 557/2016 መነሻ በማድረግ የከተማ ውስጥ አጠቃላይ የፍጥነት ገደብ በሰዓት ቢበዛ በዋና መንገዶች 50 ኪሎ ሜትር እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ በትምህርት ቤቶች፣ መኖሪያ አካባቢዎች፣ ገበያ ቦታዎች እና ሌሎች ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ በሆኑና በሚጨናነቁ አካባቢዎች ደግሞ ቢበዛ በሰዓት 30 ኪሎ ሜትርና ከዚህ ያነሰ እንቅስቃሴ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ አንዳንድ እግረኞችና አሽከርካሪዎች በጋራ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ላይ ደግሞ አሽከርካሪዎች በሰዓት 15  ኪሎ ሜትር  እንዲንቀሳቀሱ ስርዓት ተዘርግቷል፡፡

እነዚህን ህጎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችና መንገዶች የማስገንዘብ ስራም ተሰርቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር በአግባቡ ስራ እንዲውሉ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት የክትትልና ቁጥጥር ስራ መከናወኑን አቶ ክበበው ተናግረዋል፡፡

ሌላው ፍጥነትን ለማስተዳደር የተሰራው ስራ አደጋ የሚበዛባቸውን ቦታዎች በመለየት የተለያዩ የምህንድስና ማሻሻያዎች በተለይም ፈርጀ ብዙ የፍጥነት መገደቢያ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታትም ከ640 በላይ የኮንክሪት እና 6 ሺህ የፕላስቲክ የፍጥነት ማብረጃ ጉብታዎች፣ ምልክትና ማመላከቻዎችን መትከል፣ የመንገድ ደህንነትን የሚያስጠብቁ የመንገድ ላይ ቀለም ቅቦች የመሳሰሉት ተሰርተዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት አደጋ በሚበዛባቸውና የ45 ዜጎች ህይወት፣ በ2016 በጀት ዓመት የ40 ሰዎች ህይወት፣ በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ የ26 ሰዎች ህይወት ያለፈባቸው መስመሮች ላይ የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም የ19 ሰዎችን ህይወት መታደግ መቻሉን  በዳሰሳ ጥናት ማረጋገጥ  ተችሏል፡፡ የፍጥነት መገደቢያዎች በተሰሩባቸው አካባቢዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን የሞት መጠን በ16 በመቶ መቀነስ እንደተቻለም አቶ ክበበው አብራርተዋል።

ሌላው ተሽከርካሪ ከመንገድ ላይ ወጥቶ እግረኞችን እንዳይገጭ ፍጥነቱን የሚቀንስ “ሴፍቲ ሮለር” (ቢጫ አንፀባራቂ ቀለም ያለው ጠንካራ ብረት፤ ወደ መሬት ውስጥ አንድ ሜትር ከግማሽ፤ ከመሬት በላይ ደግሞ አንድ ሜትር ቁመት ያለው) በመሰራቱ የዘጠኝ ሰዎችን ህይወት መታደግ ተችሏል፡፡ ሌሎች እግረኛን ከትራፊክ አደጋ የሚከላከሉ እርምጃዎችን በመወሰድ በጥቅሉ የ37 ዜጎችን ህይወት መታደግ እንደተቻለ አቶ ክበበው ተናግረዋል፡፡  

አቶ ክበበው እንደገለፁት፣ አዲስ አበባ ያገኘችው ከሰሞኑ እውቅና እና ሽልማት የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና ከፍተኛ አመራሮች የመንገድ ደህንነት እንዲረጋገጥ አመራር በመስጠት፣ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ደግሞ በቅንጅት በመስራታቸው የተገኘ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና የተለያዩ የከተማዋ ባለድርሻ አካላት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ አጋር አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ለዚህ ምስጋና ይገባቸዋል። እውቅናው ወደፊት ፍጥነትን በማስተዳደርና የመንገድ ደህንነትን በማረጋገጥ የምንሰራውን ስራ አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

“ይህንን እውቅናና ክብር የሰጠንን ብሉምበርግ ፍላንተሮፒስን በከተማ አስተዳደራችን ስም ከልብ እያመሰገንኩ በቀጣይም መዲናችንን በሁሉም መመዘኛዎች የተሻለች አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን የበለጠ መትጋታችን ይቀጥላል።” ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ከተማዋ የፍጥነት አስተዳደርን በፈጠራ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ በማድረግ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡ በተለይም ከተማ አቀፍ አውቶማቲክ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት ስርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

አሽከርካሪዎች የተፈቀደን የፍጥነት ወሰን ጠብቀው እንዲያሽከረክሩ በራዳር በመታገዝ ሰፊ የቁጥጥር ስራ በመስራት፣ ህግ የተላለፉትን በመቅጣት፣ ፍጥነትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን በተሸከርካሪዎች ላይ በመግጠም እንዲሁም በትምህርት ቤቶችና በንግድ ቦታዎች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የመንገድ ደህንነትን በትምህርት ስርዓት ውስጥ በማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝ እና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ክበበው ተናግረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የኮሎምቢያ ዋና ከተማ በጎታም ፍጥነትን በማስተዳደር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ እንደሆነች የብሉምበርግ ፍላንተሮፒስ መረጃ ያሳያል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review