አዲስ አበባ ዘመናትን ባስቆጠረ ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የመላው አፍሪካውያን ታዛ መሆኗን አስመስክራለች፡፡ በኢትዮጵያውያን አቅምና ጥበብ የተገነባቸው ከተማዋ፣ ዛሬም በአዲስ ምዕራፍ፣ በአዲስ ገፅታ፣ ትላንትን ከዛሬ አስማምታ፣ መጨውንም ታሳቢ አድርጋ አፍሪካውያን ለበርካታ ችግሮቻቸው መፍትሔ የሚያፈላልጉባቸውን ታላላቅ ጉባኤዎች በብቃት እያስተናገደች ነው፡፡
በእርግጥም በታሪክ መንገድ ላይ ጥቂት ዓመታትን ወደ ኋላ ብንመለስ የአፍሪካ የነፃነት፣ የአንድነትና ስልጣኔ መስመር የተቀየሰባት መዲና ናት አዲስ አበባ። ለአብነትም በየዓመቱ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤም አዲስ አበባ የሁሉም አፍሪካውያን ቤት ናት የሚለውን ሀሳብ የሚያረጋግጥ መሆኑንም ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አህመድ ሰይድ ይናገራሉ፡፡
አዲስ አበባም በፍፁም ሰላም፣ በላቀ እንግዳ ተቀባይነትና ዘመኑን በዋጀ ስልጣኔ አፍሪካውያን እንደ ቤታቸው ተሰምቷቸው ልዩ ልዩ ችግሮቻቸውን የሚመክሩባት ማዕከልነቷን አስቀጥላለች። በየዓመቱ ከሚከናወነው የህብረቱ ጉባኤ ባሻገር ታላላቅ የአህጉሪቱ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ስብሰባ በተከታታይ በማከናወን ላይ መሆናቸውንም የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡
ለአብነትም የትምህርት ጥራት እና ምዘናን ለማሻሻል ያለመው አህጉራዊ ጉባኤን መጥቀስ እንችላለን። 41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ጉባዔ “የትምህርት ምዘናን ለማሸጋገር ጥራት ያለው ትምህርትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው፡፡ ይህ ዓመታዊ ጉባዔ፤ ከነሀሴ 19 እስከ ነሀሴ 23 2017 ለአምስት ተከታታይ ቀናት ተከናውኖ ትላንት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
በጉባዔው ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ ዓለም በየዕለቱ በፍጥነት ስልጣኔን ተከትላ በለውጥ ጎዳና ላይ ባለችበት በአሁን ወቅት፤ አፍሪካ የወደፊቷን በጥንቃቄ መስራት እንዳለባት ገልፀዋል፡፡
ስለ አህጉራችን መሰረታዊ እና ዘላቂነት ያለው ለውጥ መስራት ያለብን ዛሬ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በትምህርት ተደራሽነት ባለፉት 5 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ማከናወኗንም አመላክተዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ አያይዘው እንደገለጹት በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እኩል ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ ነው።
በእርግጥም የትምህርት ጥራት፣ ምዘናና ተደራሽነት የአፍሪካ ቁልፍ አጀንዳ ነው፡፡ በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርትና ስነ ባህሪ ጥናት ኮሌጅ ዳይሬክተር አሸብር ደመቀ( ዶ/ር) ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አንዳንድ ሀገራት የሀገራዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረጉ የትምህርት ስርዓቶች ቢኖሩም እንደ አህጉር ግን በትምህርት ስርዓቱ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ አልመጣም፡፡
ይህም በመሆኑ አፍሪካ በዘርፉ ያለውን መሰረተ ልማትና መሰል ችግሮች እንዳሉ ሆነው አፍሪካ ተቸግራ ያስተማረቻቸው ልጆቿ ወደ ሌሎች አህጉራት በ (Brian drain) ይፈልሱባታል፡፡ በሉላዊነት ዓለም ይህ በቀጥታ ችግር አለው ባይባልም ከኢኮኖሚያዊና ከትምህርት ስርዓቱ ጋር እንደሚያያዝ ግን ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ጥራት ችግር በአህጉሪቱ በስፋት እንደሚስተዋል የጠቆሙት አሸብር (ዶ/ር) ይህም በመሆኑ ተማረ የምንለው ሀይል ወደ ስራ ሲሰማራ ችግሩ በዚያው ልክ ይሆናል፡፡ ይህም የአፍሪካ የትምህርት ስራዓቱ ላይ ያለው ችግር በሚገባ መጠናት እናዳለበት አመላካች ነው፡፡
በመሆኑም አፍሪካውያን በአዲስ አበባ ይህንን ችግራቸውን በሚፈታ መልኩ ውይይት ማድረጋቸው አሁንም አዲስ አበባ የአፍሪካውያን ታላላቅ ጉዳዮች የመመካከሪያ ማዕከልነቷን ከፍ አድርጋ መቀጠሏን የሚያሳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ምሥረታ በፊት ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻ የሆነውን አንፀባራቂውን ፀረ ቅኝ አገዛዝ ታላቅ ድል በዓድዋ ኮረብቶች ተቀናጀች። ይህንንም ተከትሎ የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦችና ነፃነት ናፋቂዎች ዓይን ማረፊያ በመሆን በዓለም የታሪክ መዝገብ ላይ በደማቁ ሰፍራለች። ይህንንም ተከትሎ አፍሪካውያን በተደጋጋሚ “ኢትዮጵያ ሀገራችን አዲስ አበባ ቤታችን” እያሉ መስክረውላታል፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከመሆን አልፋ እንደ ኒውዮርክና እንደ ጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መናኸሪያ መሆን ችላለች፡፡ ለዚህ የበቃችውም ቀደምት ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ለሀገራቸው ክብር በከፈሉት መስዋዕትነት ነው::
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም ይህንን በታላቅ መስዋዕትነት የተገኘ ክብር በታላቅ ከፍታ ለማስቀጠል ከዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች ባሻገር ከተማዋን በዓለም አቀፍ የከተሞች መስፈርት ደረጃ ለማስቀመጥ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ታላላቅ ተቋማት ጉባኤዎቻቸውን በመዲናዋ አድርገዋል፡፡ ይህንን መሰል መድረኮች አሁንም እንደቀጠሉ መሆናቸውን የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አህመድ ሰይድ ይናገራሉ፡፡
አክለውም አዲስ አበባ ከትላንት እስከ ዛሬ የአፍሪካ አዳራሽን ጨምሮ ለአፍሪካውያን የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችን በመገንባትና በማደስ፣ ከተማዋን በኮሪደር ልማትና በልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተወዳዳሪና ተመራጭ በማድረግ ኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ አንድነት የተጫወተችውን ሚና ከፍ አድርጎ ማስቀጠል ተችሏል፡፡ ይህም በመሆኑ ዛሬም አዲስ አበባ አፍሪካውያን ልዩ ልዩ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚመካከሩባት የነፃነት አደባባይ ሆናለች፡፡
ለዚህ ደግሞ ብዙ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ትላንት ከተጠናቀቀው የትምህርት ጥራት እና ምዘናን ለማሻሻል ካለመው ጉባኤ ባሻገር ዛሬ ፍፃሜውን የሚያገኘው፣ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀልን መከላከል ቡድን ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ካሉ ታላላቅ አፍሪካዊ ጉዳዮች ከሚመከርባቸው ጉባኤዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎች ድንበር ተሻጋሪ እና የሚያስከትሉት ተጽዕኖ ዓለም አቀፍ መሆኑን የጠቆሙት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አህመድ ሰይድ አዲስ አበባ ይህንን መሰል ጉባኤ ለማከናወን መመረጧና በብቃትም ማስተናገድ መቻሏ ከተማዋ ምን ያህል አፍሪካውያንን በሚያኮራ ለውጥ ውስጥ መሆኗን የሚጠቁም ነው ብለዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አዲስ አበባ በርካታ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን እያጠናከረች ነው። የኮሪደር ልማቱ ደግሞ በመዲናዋ ሁሉን አቀፍ ተመራጭነት ላይ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡
አዲስ አበባ በተጠናቀቀው በጀት አመት ብቻ 150 ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በከፍተኛ ስኬት እንዳስተናገደች የአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ ተመላክቷል። ከተማዋ በተጠቀሰው ወቅት ብቻ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህል ጎብኝዎችን እንዳስተናገደች እና 143 ቢሊዮን ብር ያህል ሀብት ወደ ኢኮኖሚው ገቢ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
ለዚህ ከፍተኛ ውጤት መመዝገብ አዲስ የተገነቡ፣ የታደሱ ነባር ቱሪዝም መሰረተ ልማቶች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት፣ የግሉ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመንግስት የተናበበ ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸውም በመረጃው ተካቷል። ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተከናወኑ ጉባኤዎች መካከል በጥቅምት ወር ብቻ “ከረኃብ ነፃ የሆነ ዓለም” የተሰኘውን ጉባኤ መጥቀስ እንችላለን፡፡ ይህ ኮንፈረንስ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት እንደሆነም አይዘነጋም። በተጨማሪም የካፍ ጉባኤ እና የአፍሪካ መከላከያ ጉባኤ እና ሌሎች ታላላቅ አጀንዳዎች ምክክር የተደረገባቸው አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች በአዲስ አበባ መከናወናቸው በትክክልም መዲናዋ ለአፍሪካውያን ብሎም ለዓለም ታላላቅ ተቋማት የመመካከሪያ ማዕከል ሆና መቀጠሏን የሚመሰክሩ ናቸው፡፡
በመለሰ ተሰጋ