በክረምት ወቅት አዲስ አበባ ከምትፈተንባቸው ችግሮች መካከል የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ቀዳሚው ነው። ከ4 ዓመት በፊት የከተማዋ የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ይፋ ያደረገው ጥናትም ይህንኑ ያመላክታል። በወቅቱ ከ169 በላይ የከተማዋ አካባቢዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደነበሩ ጥናቱ አስፍሯል። 20 ሺህ 955 አባዎራዎችም ተጋላጭ እንደሆኑ ተመላክቶ ነበር።
በዚህ ጥናት መሠረት የአደጋ ተጋላጭነቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ በ30 ወረዳዎች ተጋርጦ ነበር፤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ወረዳ 2፣ 3፣ 4 እና 8 ከተጋላጮቹ መካከል ነበሩ። ለመሆኑ የእነዚህ አካባቢዎች አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከክፍለ ከተማው ተጋላጭ አካባቢ ነዋሪዎች እና ከክፍለ ከተማው የስራ ኃላፊዎች ባገኘነው መረጃ መሠረት የጎርፍ ተጋላጭነት ሁኔታው መቃለሉን አረጋግጧል፡፡ በተለይ በዘንድሮው የክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት፣ ቢከሰትም የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ መከላከል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ለመታዘብ ተችሏል፡፡
በእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ተስፋዬ ቀናሲ በክረምት ወቅት በጎርፍ ምክንያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በተጋላጭ አካባቢዎች ላይ የቅድመ መከላከል ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀውልናል፡፡
በክፍለ ከተማው በወረዳ 1፣ 2፣ 3፣ 4 እና 8 የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም በተለምዶ መስጂድ ሰፈር፣ መጋላ ሰፈር፣ አጂፕ፣ በሰቃ ትምህርት ቤት አካባቢ፣ ህንድ ግቢ እና ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
ከተጋላጭ አካባቢዎች መካከል አንዱ የአቃቂ ወንዝ አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ የወንዙ ውሃ መስመሩን ተከትሎ እንዲወርድ ደለል የማፅዳትና ሌሎች የማስተካከል ስራዎች በመሰራታቸው ያጋጥም የነበረው የጎርፍ አደጋ ተቃልሏል። በወረዳ 4 ገላን ኮንዶሚኒየምም በክፍለ ከተማው አስተባባሪነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን እና ቀይ መስቀል ተባብረው ወደ 600 ሜትር የሚጠጋ የድጋፍ ግንብ በመስራታቸው ችግሩ እንዲቃለል ሆኗል፡፡
በኮማንደር ተስፋዬ ማብራሪያ መሠረት፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ውስጥ የሚገኘው አጂፕ ሰፈርም ከተጋላጮቹ አንዱ የነበረ ሲሆን፣ አስር የአካባቢው አባወራዎች ከአደጋ ስጋት ነፃ ወደ ሆነ ተለዋጭ የቀበሌ ቤት ተሰጥቷቸው እንዲነሱ ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ በወረዳ 8 አቃቂ በሰቃ ትምህርት ቤት አካባቢ በተለምዶ ህንዶች ግቢ በሚባለው ሰፈርም ስድስት አባወራዎችን ከአደጋ ስጋት ነፃ በሆነ አካባቢ እንዲሰፍሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
መላው የመዲናዋ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት እንደሚጠብቁት ሁሉ በየአካባቢያቸው የሚገኙ የፍሳሽ መውረጃ መስመሮች በቆሻሻ እንዳይደፈኑ ለሚደረግ ጥሪ ተገቢ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸውም ኮማንደር ተስፋዬ አሳስበዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማናየ ጫኔ በበኩላቸው፣ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙት የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ፅዳትና አዳዲስ ዝርጋታ ስራዎች የጎርፍ ተጋላጭነት ስጋትን እየቀነሱ ነው፡፡ ይህ ተግባር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደረጃም ሊያጋጥም የሚችልን የጎርፍ አደጋ ስጋት አቃልሏል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ማናየ ማብራሪያ፣ 9 የጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎች ችግር በዘላቂነት የተፈታ ሲሆን፣ አምስቱ በዘጠና ቀን እቅድ ተካትተው እየተሰራባቸው ነው። ከገፈርሳ እና ከለገዳዲ ግድብ የሚለቀቅ ውሃ በክፍለ ከተማው ሌላ የጎርፍ አጋላጭ ምክንያት ነው፡፡ ችግሩን ለማቃለል ጊዜያዊና ዘላቂ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ የውሃ መውረጃ ቱቦዎችን ጨምሮ ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ የወንዝ ዳርቻዎችን የመጥረግ ስራ ተሰርተዋል፡፡
ወረዳ 6 ሳሪስ አካባቢ በተለምዶ ቦቼ ሰፈር ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ያለው መሰል ችግር በክፍለ ከተማ አቅም የማይፈታ በመሆኑ በሜጋ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የድጋፍ ግንብ ስራ እየተሰራለት ነው፡፡ ይህ ቦታ በአካባቢው ላሉ ነዋሪዎችም እንደከፍተኛ ስጋት የሚታይ በመሆኑ አካባቢው የወንዝ ዳርቻ ልማት ተሰርቶበት በዘላቂነት የሚለማበትና ከስጋት ነፃ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
በክፍለ ከተማው የወረዳ 12 የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ዘውዱ፣ ከዚህ ቀደም ክረምት በመጣ ቁጥር ከፍተኛ የሆነ የጎርፍ ስጋት እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን ችግር ለማቃለል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ በወረዳው ቀጠና 5 ብሎክ 7 እና ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጎርፍ የሚያጠቃቸው እንደሆኑ ጠቅሰው፣ የችግሩን አሳሳቢነት እንደወረዳ አስተዳደር በመገምገም በአቅራቢያ ያለን የኃይማኖት ተቋምና ነዋሪዎችን በማስተባበር 950 ሜትር ክፍት የጎርፍ መከላከያ ግንብ ማስገንባት ተችሏል ሲሉ አክለዋል፡፡
በክፍለ ከተማው የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት እፎይታ እንደሰጣቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተለምዶ ገላን ኮንዶሚኒየም የሚባል አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ የሺ ባህሩ በአካባቢው መኖር ከጀመሩ ከ10 ዓመት በላይ እንደሆነና ክረምት በገባ ቁጥር የጎርፍ አደጋ ስጋት ይጋረጥባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ከላይኛው የከተማዋ አካባቢዎች የሚመጣ ጎርፍ ወደ ጋራ መኖሪያው ግቢ በመግባት የእለት እንቅስቃሴአቸውን ያውክባቸው እንደነበር ጠቁመው፣ በተለይ ህፃናትና አቅመ ደካሞች ለተለያዩ ጉዳቶች ሲዳረጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ካለፈው ዓመት ወዲህ ግን የውሃ መውረጃ ቦይና የድጋፍ ግንብ በመሰራቱ ችግሩ መቃለሉንና እፎይታ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ክረምት በመጣ ቁጥር ጎርፍ ወደ ጋራ መኖሪያው በመግባት በተለይ ምድር ላይ ላሉ ወገኖች ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ላይ የጎርፍ መከላከያ በመገንባቱ ችግሩ ተቃልሏል ሲሉ አክለዋል፡፡
ወይዘሮ ቀለሟ አበራ እና አቶ ሙሉጌታ ሸመሌ በክፍለ ከተማው ወረዳ 12 በተለምዶ ሶኬ ተብሎ የሚጠራ መንደር ነዋሪ ናቸው፡፡ አካባቢው ተዳፋት ያለው በመሆኑ ዝናብ በዘነበ ቁጥር ጎርፍ ወደ ቤታቸው እየገባ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሆነው ይኖሩ ነበር፡፡ አሁን ግን በተሰራው የድጋፍ ግንብና ውሃ መውረጃ ቦይ ሳቢያ ከስጋት ተላቅቀናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በተለምዶ ክረምት ሲመጣ “የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ሁሉም ነዋሪ የፍሳሽ መውረጃዎችን በማፅዳት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ሲባል ይደመጣል። በመዲናዋ ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ በሚዘንበው ዝናብ በየአካባቢው የምንመለከተው ከፍተኛ ጎርፍ ከዚህም በላይ ስራዎችን መስራት እንዳለብን ይጠቁመናል።
ለዚህም ሲባል ክረምቱ ከመግባቱ ቀደም ብሎ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን እና ሌሎች ተቋማትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትልልቅ የውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ወንዞችን በመጥረግ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ የተዘጉ ስፍራዎችን ለውሃ መውረጃ የማመቻቸት ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በሸዋርካብሽ ቦጋለ