በካሬ ከፍተኛ ዋጋ 91 ሺህ 330 ብር፣ ዝቅተኛ 17 ሺህ 152 ብር ሆኗል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የ6ኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ አሸናፊዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
ቢሮው ይፋ ያደረገው የተጫራቾች ዝርዝር፤ ከአንድ ወር በፊት (ማለትም ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም.) በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ባወጣው የሊዝ ጨረታ ማስታወቂያ ላይ ተወዳድረው ያሸነፉትን መሆኑን ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በላከው መረጃ አሳውቋል፡፡
ለሊዝ ጨረታ ቀርበው የነበሩት በየካ፣ በኮልፌ ቀራንዮ፣ በአዲስ ከተማ፣ በጉለሌ፣ በለሚ ኩራ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሚገኙና ለተለያዩ አገልግሎቶች የተዘጋጁ የልማት ቦታዎች መሆናቸውን ያስታወሰው የቢሮው መረጃ፤ ከነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በይፋ ተከፍቶ አሸናፊዎች መለየታቸዉን ጠቅሷል፡፡
“1ኛ የወጣችሁ አሸናፊ ተጫራቾች መረጃውን የያዘው ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ባሉት አስር (10) የሥራ ቀናት ውስጥ ለም ሆቴል አካባቢ ኤም.ኤ.ህንጻ ላይ በሚገኘዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ 3ኛ ፎቅ፣ ቢሮ ቁጥር 303 በመቅረብ የሚጠበቅባችሁን በማሟላት የሊዝ ውል እንድትፈጽሙ ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡
አያይዞም፤ አንደኛ የወጡ ተጫራቾች ውል የማይፈጽሙ ከሆነ በሊዝ ደንቡ መሰረት ዕድሉ ሁለተኛ ለወጡ ተጫራቾች የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ሁለተኛ የወጡ ተጫራቾች በተመሳሳይ ውል የማይፈጽሙ ከሆነ ሦስተኛ የወጡ ተጫራቾች በሊዝ ደንብ 162/2016 እና በተጫራቾች መመሪያ ላይ በተቀመጠዉ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ቢሮው በውስጥ ማስታወቂያ ጥሪ የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል፡፡ ለጨረታ ከወጡ 132 ቦታዎች ውስጥ የቦታ ኮድ LDR-NIF-MIX-00014508 ከጨረታ መሰረዙንም አሳውቋል፡፡
በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የመሬት ሊዝ ጨረታ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክብሮም አሰፋ ስለጨረታው ሂደት እና ውጤት አስመልክቶ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቦታዎች ለጨረታ ከመቅረባቸው አስቀድሞ በተሠራው ሥራ ከይገባኛል ጥያቄ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል፣ የጨረታ ሽያጭ ሂደቱም በከተማ አስተዳደሩ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በለማ ሶፍት ዌር አማካኝነት ተከናውኗል ብለዋል፡፡
በዚህ የጨረታ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ የተመዘገቡት ቁጥራቸው 8 ሺህ 14 እንደነበር ያስታወሱት አቶ ክብሮም፤ ከእነዚህ ውስጥ የጨረታ ሰነድ የገዙት 5 ሺህ 215 ናቸው፡፡ የጨረታ ሰነዱን ከገዙት መካከል የጨረታ ሰነዱን ሞልተው የመለሱት ተጫራቾች ቁጥር ደግሞ 4 ሺህ 291 ሲሆን፤ የጨረታ ኮሚቴው የተለያዩ ማጣራቶችን አድርጎ ብቁ ናቸው ብሎ የለያቸው 3 ሺህ 568 ተጫራቾች ለጨረታ ለቀረቡት 132 ቦታዎች እንዲወዳደሩ ተደርጓል፡፡
የጨረታ አሸናፊዎችን ለመለየት የሚያስችለው የመጨረሻ ተግባር በሦስት ቀናት ውስጥ መከናወኑን ያነሱት የኮሚቴ ሰብሳቢው፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ቦታ ለጨረታ ያቀረቡት (ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 56 ቦታዎች፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 45) እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ቀን እንዲሁም ሌሎቹ አምስት ክፍለ ከተሞች በአንድ ቀን መከናወኑን አብራርተዋል፡፡ ሥራው በቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ፣ በአዳራሽ ውስጥ ለተጫራቾች ግልፅ ተደርጎ በአዳራሽ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
በ6ኛው ዙር በተካሄደው የመሬት ሊዝ ጨረታ ከቀረቡት ቦታዎች መካከል በአቃቂ ቃሊቲ ለሚገኝ ቦታ በካሬ 91 ሺህ 330 ብር ዋጋ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በተመሳሳይ በዚሁ በክፍለ ከተማ ለሚገኝ ቦታ በካሬ 17 ሺህ 152 ብር በመቅረብ ዝቅተኛ ሆኖ መመዝገቡን የኮሚቴው ሰብሳቢ አብራርተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ቢሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቦታዎች ለጨረታ ማቅረቡን እንደሚቀጥል አቶ ክብሮም አሳውቀዋል። እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት 80 ሄክታር የሚሆን መሬት ለጨረታ የማቅረብ ዕቅድን ይዟል፡፡ ይህን ለማሳካት ልዩ ጨረታን ጨምሮ ቁጥራቸው ስምንት የሚደርሱ ጨረታዎችን ለማከናወን አቅዷል፡፡ የ6ኛው ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ የበጀት ዓመቱ አንድ ሥራ ተብሎ የሚያዝ ሲሆን፤ በቅርቡ 7ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በደረጀ ታደሰ