የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማ የማድረግ ጥረት

You are currently viewing የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማ የማድረግ ጥረት

ለአገልግሎት በሄዱባቸው ተቋማት በፍጥነት መስተናገዳቸውን ግብር ከፋዮቹ ገልፀዋል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ተቋማት ከመደበኛው ባሻገር ማህበረሰቡን ለምሬትና ለእንግልት የሚዳርጉ አሰራሮችን የሚቀርፉ፣ ፈጣንና ውጤታማ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ተግባራትን በአጭር ጊዜ ዕቅድ ውስጥ በማካተት በተለየ ሁኔታ መከወን ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ከተማ አስተዳደር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የ90 ቀናት እቅዶችን በልዩ ሁኔታ አዘጋጅቶ ከቢሮ እስከ ወረዳ ድረስ በማውረድ እንዲተገበር እያደረገበት ያለው ልምድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ መሆኑ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎችን አስገኝቷል። ለማህበረሰቡ የሚቀርበው አገልግሎት እንዲሻሻል የማይናቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ በማበርከት ላይም ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ፤ ሁሉም ተቋማት የ90 ቀናት ዕቅድ አዘጋጅተው እንዲተገብሩ እንደ ከተማ አስተዳደር በወረደው አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የ90 ቀናት ዕቅድ እና ዕቅዱን ለመከወን የሄደበት ርቀት ላይ ዳሰሳ አድርገናል፡፡ 

አቶ አየለ ብስራት ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፤ ወረዳ 14 ነው፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ሽያጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፤ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ ናቸው። የዝግጅት ክፍላችን ያገኛቸው፤ ወደ ወረዳ 14 የማይክሮ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አገልግሎት ለማግኘት በመጡበት አጋጣሚ ነው። እሳቸው በጽህፈት ቤቱ ያገኙትን አገልግሎት የገለጹት፤ “ባለሙያዎቹ በጥሩ ሁኔታ ተቀብለው ነው ያስተናገዱኝ። ስለመጣሁበት ጉዳይ ከነገርኳቸው በኋላ፤ አገልግሎት ለማግኘት ዲጂታል የብሔራዊ መታወቂያ መያዝ ግዴታ መሆኑን ገለፁልኝ፡፡ እኔም አስቀድሜ መረጃ ስለነበረኝ መታወቂያውን ጨምሮ የተደራጀ ሰነድ በማዘጋጀት ነው የቀረብኩት፡፡ ይህንንም በማድረጌ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት አግኝቼ ጨርሻለሁ” በማለት ነው፡፡

ማንኛውንም አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋማት ሲያቀኑ፤ የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ በእጃቸው ይዘው የመንቀሳቀስ ልምድ እንዳላቸውም አክለዋል፡፡

“ገና ከበር ስንገባ ግልፅ የሆነ ‘ወዴት መሄድ ይፈልጋሉ?’ የሚል መረጃ ሰጪ ቦርድ አለ፡፡ እዚህ ላይ የሠፈሩት ጽሑፎች ተገልጋዩ የመጣበትን አገልግሎት ለማግኘት መሰረታዊ መረጃዎች የሚሰጡ ናቸው፡፡ ይህ በፍጥነት ተስተናግጀ ለመውጣት የራሱን እገዛ አድርጎልኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጽህፈት ቤቱ ተገልጋይ ሲበዛ ወረፋ ይዞ የሚጠባበቅበት ማረፊያ ወንበሮች አሉ፡፡ ተገልጋዮች ወረፋ እንደደረሳቸው መስተናገድ የሚችሉበትን ፎርም በመሙላት እንደየጉዳያቸው ይፈጸምላቸዋል፡፡ እኔም ይህንን ሂደት ነው ያለፍኩት፡፡” ሲሉም አገልግሎቱ ስለሚሰጥበት መንገድ አብራርተዋል፡፡

በወረዳው የማይክሮ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ለማ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፣ በ90 ቀናት ታቅዶ እየተከናወነ ያለው በአገልግሎት አሰጣጡ  ግብር ከፋዩን ከእንግልት እና ከአላስፈላጊ ምልልስ ለመታደግ ታሳቢ ያደረገ የአሰራር ስርዓት በመከተል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ግብር ከፋዩ ገና ወደ ጽህፈት ቤቱ እንዳቀና በቅድሚያ ሊያሟላቸው ስለሚገቡ መዘርዝሮች በግልፅ የሚያውቅበትን አግባብ በባነር፣ በብሮሸር እንዲሁም በበራሪ ወረቀት አማካኝነት የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡

የ90 ቀናት እቅድ ለማሳካት ሲታሰብ የደረጃ ሀ፣ ለ እንዲሁም ሐ ግብር ከፋዮች በንቃት ግብራቸውን እንዲከፍሉ ማስቻል ነው፡፡ በተለይም በአጭር የፅሑፍ መልዕክት እንዲደርሳቸው በማድረግ በግብር መክፈያ ጊዜ ከሚፈጠር ግርግር ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻል በማሰብ የተዘጋጀ የአሰራር ስርዓት ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎት የምንሰጥባቸውን ቢሮዎች በማፅዳት፣ በማስተካከል ብሎም በማስዋብ ለአሰራር ስርዓት ምቹ የማድረግ ስራ መሰራቱንም አስረድተዋል፡፡

ሌላኛውን ቅኝት ያደረግነው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 የማይክሮ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ነው፡፡ ወይዘሮ ሰላም አትክልቲንም ያገኘናቸው የተለያዩ የወጥ ቤት እቃዎች ንግድ ላይ የተሰማሩ ሲሆን የደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ ናቸው፡፡ በጽህፈት ቤቱ አገልግሎት ለማግኘት በመጡበት ወቅት እንደነገሩን “ወደ ተቋሙ ስመጣ ባለሙያዎች ተገቢውን መረጃ በተረጋጋ አግባብ በማስረዳት በጥሩ ሁኔታ ተቀብለው አስተናግደውኛል። የቢሮ አደረጃጀቱ ለተገልጋዩ የሚመች በተለይ የግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ስራ የሚያቀል ሆኖ አግኝቼዋለሁ” በማለትም ስለመስተንግዶው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ አስካለ ግርማ በበኩላቸው እንዳስረዱት፣ የ90 ቀናት እቅድ ማዘጋጀት እና ወደ ስራ መግባት መቻላችን  “የትኛውን ስራ በአግባቡ ፈፅመናል? የትኛውንስ ማሳካት ተቸግረናል?” በማለት በቶሎ ወደ መፍትሔ ለመግባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡ በተለይ የፋይዳ መታወቂያን (የዲጂታል መታወቂያ›) ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉ አንድ ግብር ከፋይ ህጋዊነቱን የሚያረጋግጥለት ነው። በዚያም መሰረት አንድ ግብር ከፋይ እንደ አንድ መስፈርት የሚታይ መሆኑን ተከትሎ በዚያ ልክ መረጃውን አሟልቶ እንደሚመጣ ይታወቃል ብለዋል፡፡  አላስፈላጊ ፋይሎች፣ ዕቃዎች ተለይተው እንዲወገዱ በማድረግ የቢሮውን አደረጃጀት ለአገልግሎት አሰጣጥ በሚያመች መልኩ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ስለመገባቱም ኃላፊዋ አክለዋል፡፡

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ90 ቀናት ውስጥ ትኩረት ተደርጎባቸው ከሚፈፀሙ ተግባራት መካከል ከገቢ አሰባሰብ ጋር የተያያዘው አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው፤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የ90 ቀናት እቅድን አስመልክቶ በተዘጋጁ መድረኮች ላይ፤ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እና በገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ የሚነሱ ችግሮችን መቅረፍ ቁልፍ ተግባር መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ሲናገሩ የሚደመጡት፡፡

ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም “ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እና በገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ የሚነሱ ችግሮችን መቅረፍ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ” መሆኑን በሚያስገነዝብ ከተማ አቀፍ የንቅናቄ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ከንቲባዋ፤ ይህ ስራ በሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማት በትኩረትና በተቀናጀ አግባብ መከናወን እንዳለበት የሚያሳስብ አቅጣጫዎችን መሰጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ መድረክ ላይ በአዲስ አበባ ውስጥ እየተመዘገበ ላለው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ ገቢን የመሰብሰብ እና የተሰበሰበውን ገቢ ለልማት የማዋል ብቃት እየዳበረ መምጣቱ መሆኑ ተገልጿል።

የ2017 በጀት ዓመት ያልተሰበሰበ ቀሪ ገቢን ፍትሐዊ በሆነ አግባብ አጠናቅቆ መሰብሰብ ለ2018 የከተማ አስተዳደሩ ስኬታማ የሥራ እንቅስቃሴ መሰረት መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፤ ይህም ይሳካ ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካል ተናብቦ እና ተቀናጅቶ መስራት ይገባዋል፡፡ ለ2018 በጀት ዓመት አመቺ የግብር አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋት፣ ግብር ከፋዩን ማበረታታት እና ሠራተኛውን ማትጋት ላይም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፤ ቢሮው የ90 ቀናት እቅዱን ከሰኔ ወር አንስቶ እስከ ጷጉሜን ድረስ ለመከወን ከማዕከል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር አቅዶ በስራ ላይ ይገኛል፡፡ ዕቅዱን መተግበር ከጀመረበት ቀን አንስቶ የሠራቸው ሥራዎች አበረታች ናቸው። በተለይ በንግዱ ማህበረሰብ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሄደበት ርቀት ተስፋ ሰጪ ውጤት ያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ሰውነት አክለውም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ፍትሐዊ የንግድ ስርዓት በመዘርጋት፣ በንግዱ ማህበረሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ አሰራሮችን መተግበር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ እነዚህን አሰራሮች አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ምክር ቤት አመራሮች እና የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣንን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ይህም በቢሮው የተያዘውን የ90 ቀናት ዕቅድ ለማሳካት መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡

እንደ አቶ ሰውነት ገለፃ፤ ከግብር ማሳወቂያ ጊዜ ጀምሮ ፍትሐዊ የግብር አሰባበሰብ ስርዓትን ለመዘርጋት፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል፣ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እና ከግብር ከፋዮች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡

በተጨማሪም፤ አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ተግባር ለማስገባትና የሚደረገውን ጥረት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማልማት እና ወደ ተግባር የማሸጋገር ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይህም የንግዱ ማህበረሰብ ከባለሙያዎች ስነ ምግባር፣ ከሌብነትና ብልሹ አሠራር፣ ከፍትሐዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት አኳያ የሚነሱ ቅሬታዎችን በአግባቡ ሰብስቦ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማስቻሉን ያነሱት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ረገድ የግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የስራ እንቅስቃሴ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የካሜራ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ  ማብራሪያ፤ ይህ ቴክኖሎጂ በቢሮው ስር የሚገኙ የሁሉንም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የሥራ እንቅስቃሴ ከማዕከል ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው፡፡ የሰርቪሊያንስ ካሜራ ቴክኖሎጂ በሁሉም ቅርንጫፎች የሰራተኞች የስራ እንቅስቃሴ፣ የግብር ከፋዮች መስተንግዶና አገልግሎት አሰጣጥን ለመከታተል፣ ችግሮች ሲስተዋሉም ለማረም የሚያግዝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ካሜራው ከማዕከል ሊተላለፉ የሚገባቸው መረጃዎችን በተመሳሳይ ሰዓት፣ ለሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለማድረስ ያስችላል፡፡ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በመከታተል እንዲታረሙ፣ አንዱ ከአንዱ እንዲማር እና ስህተት እንዳይደገም ያስቻለ ነው፡፡

እንደ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ90 ቀናት እቅዱ ተግባራዊ ካደረጋቸው ስራዎች መካከል ልዩ ኮድ የተካተተበት ዩኒፎርም የለበሱ የቁጥጥር ባለሙያዎች አንድ ግብር ከፋይ የሚጠበቅበትን ግብር ስለመክፈሉ የሚያረጋግጡ እንዲሁም በግብይት ወቅት ደረሰኝ ስለመቆረጡ ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎች ወደ ስራ ማስገባት ይጠቀሳል፡፡ የዚህ ተግባር ዋና ዓላማው በቢሮው የተመደቡ ሕጋዊ የቁጥጥር ባለሙያዎችን ግብር ከፋዩ በግልፅ እንዲያውቃቸው ማስቻል ነው። ይህ ሥራ በመከናወኑ ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ቦታዎች በተለይም በመርካቶ አካባቢ የቁጥጥር ባለሙያዎችን በመመሳሰል የታየውን ክፍተት ማስቀረት ተችሏል፡፡ የቁጥጥር ባለሙያዎች ለቁጥጥር በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሚስጥራዊ ቁጥር የተካተተበት መታወቂያ መያዝ እና ለግብር ከፋዩ በግልፅ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ቢሮው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለግብር ከፋዮች ምቹ የስራ አካባቢን ማዘጋጀት የ90 ቀናት ዕቅዱ አካል በማድረግ የፈፀመው ሌላኛው ተግባር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በሥሩ አንድ ከፍተኛ፣ 5 መካከለኛ፣ 11 አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አሉት፡፡ በእነዚህ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ቁጥር ደግሞ ከ7 ሺህ በላይ ነው፡፡ ወደ እነዚህ ተቋማት ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ተገልጋዮች ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ  በአገልግሎት አሰጣጡ ወቅት ተቋማቱ ለሠራተኛው እና ለተገልጋዩ ማህበረሰብ የተመቹ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተመቻቸ የስራ ከባቢ ውስጥ የሚሰጥ አገልግሎት ስኬታማ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ስለሆነም በቢሮው ስር ያሉ ሁሉንም ተቋማት ለሥራ ምቹ እንዲሆኑ የማድረጉ ተግባር በ90 ቀናት ዕቅድ ውስጥ ተይዞ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁን ባለው ሥራም አበረታች ውጤት ታይቷል፡፡ 

የ90 ቀናት እቅዱን ተፈፃሚ ለማድረግ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አላስፈላጊ ፋይሎችን እና ዕቃዎችን የማስወገድ ስራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲሽን ስራዎችን በመስራት ቢሮዎቹን ለአገልግሎት አሰጣጥ በሚያመች መልኩ መታደሳቸውን፣ የቀለም ስራው ሲጠናቀቅ የተቋሙን ገጽታ እንደሚቀይረው ገልጸዋል፡፡

“ብሔራዊ መታወቂያ (ዲጂታል መታወቂያ) ሁሉም ግብር ከፋይ ከሚስተናገድበት መስፈርት ውስጥ ግንባር ቀደም ቅድመ ሁኔታ ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከመረጃ ሰጪዎች አንስቶ በመስኮት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ጭምር የብሔራዊ መታወቂያ በቅድመ ሁኔታ ግብር ከፋዩ ይዞ ከመጣ ብቻ የሚስተናገድ ስለመሆኑ መረጃ ይሰጣሉ፡፡ በማህበራዊ የትስስር ገፃችን ላይም የተለያዩ የግንዛቤ መልዕክት ለማስተላለፍ የተቻለበት አግባብ አለ። ህጋዊነትን ለማስቀጠል ብሎም የአሰራር ስርዓቱ ግልፀኝነት የታከለበት እንዲሆን ብሔራዊ መታወቂያ (ዲጂታል መታወቂያ) አንዱ መሳሪያችን ነው” የሚሉት አቶ ሰውነት፣ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብም የሚጠበቅበትን መረጃ በማሟላት ጭምር ለአገልግሎት እየመጣ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮም ከሰኔ 05 እስከ ጳጉሜ 05 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የገቢ ማሰባሰብ አማራጮችን በመለየት የታቀዱትን የ90 ቀን እቅዶችን ለማሳካት እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሬት ዘርፍ የጣራና ግድግዳ ገቢን ማሳደግ፣ የሊዝ ውዝፍ ክፍያዎችን መሰብሰብ፣ ህጋዊ የንግድ ስርዓትን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ መደበኛ ገቢን ማሳደግ፣ የቫት ተመዝጋቢዎችን ቁጥር መጨመር እና ሌሎች ገቢን ከፍ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

 በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review