የጥበብ ማዕድ

You are currently viewing የጥበብ ማዕድ

በመዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት ቀናት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት ከተሰናዱ የጥበብ ስራዎች መካከል ደግሞ የመጽሐፍት ምረቃ፣ የሥዕል ዓውደ ርዕይ እና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጽሐፍት

ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ጌቱ ሥራዎቹን ከአንጋፋ ጸሐፍት ስራዎች ጋር በማጣመር “መባያ” በሚል ያሳተመው መጽሐፍ በዛሬው ዕለት ከረፋዱ 3:30 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) እንደሚመረቅ ተገልጿል፡፡

በሌላ መረጃ “ቀለም እና ምክንያት አፍታ ወጎች ከኮሪያ”  የተሰኘ መጽሐፍም ለንባብ በቅቷል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ከበደ ታዬ (ከበደ ወርቅ) ሲሆን፤ በኦንላይን የሽያጭ አማራጮች ለአንባቢያን መቅረቡ ተገልጿል፡፡ መጽሐፉ ደራሲው በደቡብ ኮሪያ ያያቸውን፣ የታዘባቸውንና ለኢትዮጵያ የተሰሩ የማስታወሻ ቦታዎችን ታሪክና ሌሎችንም ጉዳዮች የከተበበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በተያያዘም “የተፈቱ ሰንሰለቶች” የተሰኘው የደራሲና የህግ ባለሙያው ዳግማዊ አሰፋ መጽሐፍ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል፡፡ በአዲስ አበባ ካፒታል ሆቴል ሐሙስ ዕለት ተመርቆ ለንባብ የበቃው የደራሲው ሦስተኛው መጽሐፍ ጷጉሜን 1 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ በሐዋሳ እንደሚመረቅ ተነግሯል፡፡ መጽሐፉ የ“አዲስ ሕይወት”ን እና የ“ከማዕዘኑ ወዲህ” ተከታይ ሲሆን፤ አዳዲስ ሀሳቦችና ልምዶች የተካተቱበት እንደሆነ ተገልጿል። “ሰዉ ሙሉ ትዝታ-ወል መካ” የግጥም መድብልም በነገው እለት ከቀኑ ከ9፡00 ሰዓት ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው በዋልያ መጽሐፍ መደብር  እንደሚመረቅ ተገልጿል፡፡ ደራሲው ኪሩቤል ዘርፉ በጦቢያ ግጥም በጃዝ መድረክ ላይ የተለያዩ ስራዎችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡

በሌላ የመጽሐፍ መረጃ ከወራት በፊት ታትሞ ለአንባቢያን የደረሰው እና የጋዜጠኛ ዋለልኝ አየለ የመጀመሪያ ስራ የሆነው “የብሌን አንዳች” መጽሐፍ የፊታችን አርብ አራት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዳራሽ  ይመረቃል ተብሏል፡፡ በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ፣ ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ አምባሳር ዲና ሙፍቲን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ደራሲዎች እና ገጣሚያን የሚገኙ ሲሆን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎችም እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡

ሥዕል

ሰዓሊ እና መምህር እሸቱ ጥሩነህ በዛሬው ዕለት “የኢትዮጵያን ታሪክ በሥነ ጥበብ” በሚል ርዕስ ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ተነግሯል፡፡ መርሃ ግብሩ የሚካሄደው አራት ኪሎ ከቱሪስት ሆቴል ወረድ ብሎ ከፖስታ ቤቱ ጎን በሚገኘው ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ህንጻ 3ኛ ፎቅ ላይ  ከ4፡00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን መግቢያው በነጻ ነው፡፡

በሌላ መረጃ ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ የተከፈተው የጥበብ ዓውደ ርዕይ  ሊጠናቀቅ 4 ቀናት ቀርተውታል። በዚህ የቡድን የጥበብ ዓውደ ርዕይ ሥራዎቻቸውን እያቀረቡ ካሉ ከያኒያን መካከል ታደሰ ባይሳ፣ ሚኪያስ ሰለሞን፣ ቤርሳቤህ አለማየሁ፣ ምህረት እሸቱ፣ ዳግማዊ ጸጋዬ፣ ሱራፌል መክብብ ይገኙበታል፡፡ ዓውደ ርዕዩ የፊታችን ነሐሴ 28 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ሲሆን እየታየ ያለው በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚገኘው የፈንድቃ የባህል ማዕከል  ነው፡፡

የውይይት መድረክ

“አውደ ፋጎስ” የውይይት መድረክ የተለያዩ ሀሳቦችን እያንሸራሸረ 67ኛው ዙር ላይ ደርሷል፡፡ ነገ በሚካሄደው የውይይት መድረክ ላይ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና አርቲስት የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ናቸው፡፡

የውይይቱ ርዕሰ ጉዳይ “እይታዊ ተግባቦት፣ ቴክኖሎጂና አማራጭ መንገዶች” የተሰኘ ሲሆን ከቀኑ 8:00 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ይካሄዳል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review