ሥዕል የአንድን ሀገር ማንነት አጉልቶ በማሳየት ረገድ አበርክቶው ትልቅ ነው። ታሪካዊ ክስተቶች፣ ባህል፣ የአለባበስ ሁኔታ፣ በዓላትንና የዕለት ተዕለት ሕይወትን ይመዘግባል፣ ይተርካል፣ ለተቀረው ዓለም ያስተዋውቃል። ለምሳሌ፡- ቀደምት ሥዕሎች ስለ ቅድመ አያቶቻችን አኗኗር፣ ድል እና የትግል ዋጋ መረጃ በመስጠት ላይ ናቸው፤ በሚፈለገው ልክ ነው ለማለት ባያስደፍርም።
በተጨማሪም ሥዕሎች የሀገርን የተፈጥሮ ውበት፣ የሰዎች መልክና የኑሮ ዘይቤ ያሳያሉ። አንድ ሥዕል የመልክዓ ምድርን ውበት፣ የከተሞችን ገጽታ ወይም የገጠርን ሕይወት በሚያሳይበት ጊዜ ተመልካቹ የሀገሪቱን ገጽታ በቀላሉ እንዲረዳ ያስችለዋል ይላል፤ ሀገርኛ ይዘት ያላቸውን ስዕሎች እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የስዕል ስራዎችን በመስራት የሚታወቀው ሰዓሊ ቢኒያም አበበ።
ዘመናዊ ሥዕሎች ደግሞ የሀገርን የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የከተሜነት መስፋፋትና የማኅበራዊ ለውጦችን በማንፀባረቅ የሀገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ ያሳያሉ፡፡ ኢትዮጵያም በስዕል ጥበብ ቀደምት ከሚባሉና ራሳቸውን ለዓለም በስዕል መግለጽ ከሚችሉ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ነች፡፡
እንደ ቢኒያም ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ሥዕሎች፣ በተለይ የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎችና ጥንታዊ ቅርሶች፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን የበለፀገ ታሪክና መንፈሳዊ ቅርስ በማስተዋወቅ በኩል እጅግ ጠንካራ ናቸው።
እንደ ሰዓሊ ቢኒያም ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ሥዕሎች የራሳቸው ቀለምና መገለጫ እንዲሁም የአሳሳል ዘይቤ ቢኖራቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያገኙት እውቅና እና የሀገሪቱን ገጽታ ከማስተዋወቅ አንጻር ያበረከቱት ሚና ብዙ የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ብዙ የኢትዮጵያ የስዕል ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ጋለሪዎችና ሙዚየሞች ውስጥ እንዲታዩ የማድረግ ክፍተት መኖሩ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የጥንታዊ ሥዕሎቻችንን ያህል፣ የዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥዕል ለዓለም አቀፍ ትኩረት አልበቃም። ይሁን እንጂ አሁን ላይ በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አርቲስቶች የኢትዮጵያን አዲስ እና ዘመናዊ ገጽታ የሚያንፀባርቁ ሥራዎችን በመስራት የዓለምን ትኩረት መሳብ ይችላሉ።
ለአብነትም ሰዓሊዎች በቅርብ ጊዜ የተሰሩ እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አንድነት ፓርክ፣ ኮሪደር ልማት የመሳሰሉትን በሥዕል ከማንጸባረቅና ለውጭው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ያላቸው ሚና ወሳኝ ነው።
ሰዓሊዎች የፕሮጀክቶቹን ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ፋይዳ የሚያንፀባርቁ ሥዕሎችን መስራት አለባቸው። ለምሳሌ፡- የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ የዓድዋን ጦርነት መንፈስ፣ ጀግንነትና አንድነት የሚያሳዩ ሥራዎች ሊሠሩ ይችላሉ።
ለዓለም አቀፍ ተመልካቾች እንዲመች በእንግሊዝኛ ወይም በሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የስዕሎችን ትርጉም የሚገልጹ ጽሑፎችን ማዘጋጀት ይገባል የሚለው የስዕል ባለሙያው፣ ሥራዎቻቸውን በዲጂታል መድረኮች (እንደ ኢንስታግራም፣ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ) እና ገጸ-ድሮች ላይ ማስተዋወቅ የኢትዮጵያን አዲስ መልክ ለዓለም ለመግለጥ ያስችላል።
በተጨማሪም ከውጭ ሀገር ጋለሪዎች፣ ሙዚየሞችና አርቲስቶች ጋር በመተባበር የጋራ ኤግዚቢሽኖችና የሥዕል አውደ ርዕዮችን ማዘጋጀት፣ በእነዚህ ፕሮጀክቶች አነሳሽነት የተሠሩ ሥዕሎችን እንደ ፖስተር፣ ካርድ፣ ቲሸርትና ሌሎች የስጦታ ዕቃዎች በማዘጋጀት ለጎብኚዎች ማቅረብ የሀገራችንና የከተማችን አዲስ አበባን ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ይረዳል። ምክንያቱም ብዙ ሀገሮች ሥዕልን ባህላቸውንና ማንነታቸውን ለማስተዋወቅ በተሳካ ሁኔታ ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ፡- የፈረንሳይ ሉቭር ሙዚየም የሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሥዕልና የኪነ ጥበብ ታሪክ ያሳያል። ይህ ሙዚየም በዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን በመሳብ ለፈረንሳይ ታላቅ የገቢ ምንጭ ከመሆኑም በላይ የፈረንሳይን የኪነ ጥበብ ልዕልና የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በጃፓንና በሜክሲኮ ያለው የስዕሎች አበርክቶም በተመሳሳይ የሚገለጥ ፋይዳ ያላቸው ናቸው በማለት ሰዓሊ ቢኒያም ለኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ዓለም አቀፍ ልምዶችን ይጠቅሳል፡፡
ኢትዮጵያም በዓድዋ ሙዚየም ውስጥ እንደሚገኘው የስዕል ጋለሪ፣ በእንጦጦ የተከፈተው የሥነ ጥበብ ማዕከል… ሁሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሙዚየሞችና ጋለሪዎችን በመገንባት የኢትዮጵያን ገጽታ በሥዕሎች ለዓለም ማሳየት ትችላለች ይላል ወጣቱ ሰዓሊ።
ሥዕሎችን ዲጂታል በማድረግና የኦንላይን ማኅደሮችን በመፍጠር በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ሥዕሎችን ከቱሪዝም ኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ጎብኚዎች የኢትዮጵያን ሥዕል እንዲያደንቁና እንዲገዙ ማበረታታት እና የኢትዮጵያን ሥዕሎች በዓለም አቀፍ የባህል ዝግጅቶችና ኤግዚቢሽኖች ላይ በማቅረብ የኪነ ጥበብ ዲፕሎማሲን መጠቀም ከዘርፉ አትራፊ ለመሆን መሰራት ያለባቸው ስራዎች መሆናቸውን አክሏል።
ይህ ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያን ባህል፣ ማንነትና አዲስ ገጽታ የሚያንጸባርቁ እና የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ሥዕሎችን መስራት፣ የኢትዮጵያ ሥዕሎች የሚሸጡባቸው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የኦንላይን ሽያጭ (e-commerce plat forms) መፍጠር ወይም ያሉትን መጠቀም፣ የሀገር ውስጥ ሥዕል ጋለሪዎችን ማጠናከርና የሥዕል ገበያዎችን ማስተዋወቅ በስፋት ያልሰራንበትና ሌሎች ሀገራት የተጠቀሙበት መንገድ ነው፡፡
ይህን አስተያየት የስዕል ስራዎችን ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኡጋንዳ፣ በሴኔጋል እና ሮማንያ የስዕል ስራዎቹን ለእይታ ያበቃው ሰዓሊ ብርሃኑ ማናየም ይጋራዋል፡፡
“በሌሎች ሀገራት ያየሁት ተሞክሮ እንደ ሀገር ብዙ መስራት እንዳለብን ነው፡፡ ጥበብ ባህል ነው፡፡ ሰውና ባህል ደግሞ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ መንግስትም ይህን በመረዳት ድጋፍ ያደርግላቸዋል። ከተለያዩ ሀገራት ሰዓሊዎችን በመጋበዝ አውደ ርዕይ እንዲዘጋጅ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ከተለያዩ ሀገራት ብዙ የጥበብ ሰዎች ስለሚመጡ ገቢ ለማግኘት፣ ገጽታን ለመቀየርና ልምድ ለመለዋወጥ ይረዳል” ሲል በሌሎች ሀገራት የታዘበውን ያጋራው ሰዓሊ ብርሃኑ፣ በእኛም ሀገር ይህ ቢለመድ እጅግ በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርቷል፡፡
የአርታዊ ጋለሪ መስራቾች ከሆኑት አንዱ የሆነው አብነት ተሾመ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በሰጠው አስተያየት እንደገለጸው፣ አዲስ አበባ ብዙ የጥበብ ማሳያ ቦታ ቢኖራት የበለጠ ትጠቀማለች፡፡ ሰዎች በሚያማምሩ ጎዳናዎች የእግር መንገድ አድርገው ስዕል የሚያዩበት ሁኔታ ቢጨምር ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
“የውጭ ጎብኚዎች ወደ እኛ ጋለሪ ስዕል እና ፎቶ ግራፍ ለመመልከት ሲመጡ፣ ስለአዲስ አበባ ለውጥና አዲስ ገጽታ ይገረማሉ፡፡ ከአዳዲስ ልማቶች ጋር “የስዕል ጋለሪዎች በብዛት ቢኖሩ” የሚል አስተያየትም ይሰጣሉ፡፡ እኛም ለስራ ወደ ጀርመን ባቀናንበት ወቅት ያየነው በአንድ ትንሽ ከተማ በርካታ የስዕልና የፎቶ ግራፍ ማሳያ ማዕከላት መኖራቸውን ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ለስራ ፈጠራ፣ ለገጽታ ግንባታ፣ ለባህል እድገት፣ ስልጣኔን እና የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ተጠቅመውበታል” ብሏል፡፡
በተጨማሪም ውጭ ሀገር ስዕል የሚያሳዩና የሚሸጡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ሰዎች አሉ፡፡ በሄዱበት ሀገር ስዕል ሲሸጡ እና ሲያሳዩ ታክስ ለዚያ ሀገር መንግስት ይከፍላሉ። መንግስትም ለዘርፉ ትልቅ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በእኛ ሀገር ለስዕል ማሳያ ቦታ ሰፊ ትኩረት ቢሰጥ ኢትዮጵያም እንደዚህ አይነት አሰራር ቢለመድ ሌላኛው የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚችልና ወደ ውጭ እንደሚላኩ ሌሎች ምርቶች ትልቅ ገቢ መፍጠር፣ ለገጽታ ግንባታም ትልቅ አቅም መሆን ይችላል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከላይ እንደተጠቀሰው ሌሎች ሀገራት በስዕል ሀያልነታቸውን ያሳያሉ። ባህላቸውን ለሌላው ይገልጻሉ፡፡ የከተሞቻቸውን ውበትና ገጽታ ለተቀረው ዓለም ያስተዋውቁበታል፡፡ ለመሆኑ ሀገራችን ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማን ምን ይጠበቃል? የሚለውን ጥያቄ ሰዓሊ ቢኒያም ሲመልስ፣ በመጀመሪያ መንግስት ለሥዕል ዘርፉ ድጋፍ መስጠት፣ ሙዚየሞችን ማጠናከርና ዓለም አቀፍ የማስተዋወቅ ሥራዎችን መምራት አለበት። ሕጎችና አሠራሮች ሥዕሎችን ወደ ውጭ ለመላክ የተመቹ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ሰዓሊዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ማሳደግ፣ አዳዲስ ቴክኒኮችን መማርና የዓለምን ገበያ የሚያሟሉ ሥራዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል። በመዲናችን የሚሰሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በስዕል ስራዎቻቸው ውስጥ ማካተትና ወቅቱን የዋጁ ጥበባዊ ስራዎችን በመሳል ተዋዳዳሪ መሆን አለባቸው፡፡ እንዲሁም ሥራዎቻቸውን በብቃት እንዴት ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ቢማሩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሰዓሊ መሆን ይችላሉ። በእነሱ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ገጽታ ለዓለም ይታያል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የባህል ተቋማትና ጋለሪዎች የኢትዮጵያን ሥዕል ለማስተዋወቅ የሚረዱ የተለያዩ ዝግጅቶችንና ኤግዚቢሽኖችን ማዘጋጀት አለባቸው። እንዲሁም የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የስዕል ገበያዎችን ማገናኘት ይጠበቅባቸዋል።
ባለሀብቶችና ስፖንሰሮች በሥዕል ዘርፉ ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ ለሥዕል ጋለሪዎችና ለአርቲስቶች ድጋፍ በመስጠት የዘርፉን ዕድገት ማገዝ፣ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታም ለዓለም በማስተዋወቅ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይችላሉ ሲል በማጠቃለያ ሃሳቡ አንስቷል።
በጊዜው አማረ