ልጆች፤ ከጨዋታ በኋላ ምን ያህል እጃችሁን የመታጠብ ልምድ አላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፤ ከጨዋታ በኋላ ምን ያህል እጃችሁን የመታጠብ ልምድ አላችሁ?

ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? የክረምት እረፍት ጊዜያችሁን እንዴት እያሳለፋችሁ ነው? “በመጫወት፣ በመዝናናት…” እንደምትሉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ጥሩ። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ እናንሳላችሁ፤ “ከጨዋታ በኋላ እጃችሁን የመታጠብ ልምዳችሁ ምን ይመስላል?” ይህንን የጠየቅናችሁ አንዳንድ ልጆች ከጨዋታ በኋላ በመቸኮል፣ በመርሳት ወይም ግድየለሽ በመሆን እጃቸውን ሳይታጠቡ የሚመገቡ ስላሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም እጅን ሳይታጠቡ መመገብ ለተለያየ በሽታ ያጋልጣል፡፡ በጉዳዩ ላይ እርስ በእርስ ተወያዩ፡፡ እኛ ደግሞ ያነጋገርናቸውን ልጆች እንዲሁም የጤና ባለሙያ ምክር እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

ዮናስ ጸጋዬ የ12 ዓመት ልጅ ነው፤ ያገኘነው ደግሞ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በሚገኘው ረጲ ጃፓን የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለምዝገባ በመጣበት ወቅት ነው፡፡ የ7ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ህጻን ዮናስ ብዙውን ጊዜ በክረምትም ሆነ በበጋ ወራት እግር ኳስን አዘወትሮ፣ ብይ ደግሞ አልፎ አልፎ እንደሚጫወት ነግሮናል፡፡

“ከጨዋታ በኋላ በተለይም ምግብ ልመገብ ስል ሁልጊዜ እጄን በውሃና ሳሙና የመታጠብ ልምድ አለኝ፡፡ በአንድ ወቅት ንጽህናው ባልተጠበቀ እቃ ተመግቤ ታምሜ አውቃለሁ። ይህም  ንጽህናን አለመጠበቅ የጤና ችግር እንደሚያስከትል እንድረዳ አድርጎኛል። ምንም አይነት ምግብ ቤቴም ሆነ ትምህርት ቤት እጄን ሳልታጠብ አልመገብም፡፡” ብሏል፡፡

የ13 ዓመቱ ልጅ አቡበከር ከድርም በተመሳሳይ ልምድና ተሞክሮውን ነግሮናል፡፡ “ቁርሴን፣ ምሳዬን እና እራቴን የምመገበው እጄን ታጥቤ ነው። ከቤቴ ለመጫወት ከወጣሁ ስመለስ እጄን ብቻም ሳይሆን ፊቴንና እግሬንም ጭምር የመታጠብ ልምድ አለኝ፡፡ አንድ ቀን ተጫውቼ ወደ ቤቴ ከገባሁ በኋላ ሳልታጠብ እረፍት ለማድረግ ብዬ ተኛሁ። ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ከእንቅልፌ ስነሳ ምሳ ቀርቦ ስለነበር መታጠብ እንዳለብኝ በመዘንጋት ተመገብኩ፡፡ ትንሽ እንደቆየሁ ሆዴን ቆረጠኝ፡፡ ቁርጠቱ ወደ ተቅማጥ ተቀይሮ ታመምኩ፡፡ በወቅቱ ታክሜ ነው የዳንኩት፡፡ ይህ ችግር ካጋጠመኝ በኋላ በቤት ውስጥም ሆነ በትምህርት ቤት ሳልታጠብ አልመገብም፡፡ ታናሼንም ንፅህናውን እንዲጠብቅ እመክረዋለሁ፡፡” ሲል አስተያየቱን ገልጿል፡፡       

ከንጽህና ጉድለት በተለይም፤ እጅን ባለመታጠብ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች እና ልጆች ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄ ምን እንደሆነ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬተር ዶክተር ሚኪያስ ተፈራ ለልጆች መልዕክት እንዲያስተላልፉ አድርገናቸዋል፡፡

“ልጆች በጨዋታ ጊዜ አፈርን ጨምሮ የተለያዩ ቆሻሻ ነገሮችን ከነካችሁ በኋላ ሳትታጠቡ ከተመገባችሁ እንደ ባክቴሪያ፣ ፓራሳይት ለምሳሌ ጃርዲያ፣ የሆድ ትላትል፣ ታይፎይድ፣ ታይፈስ፣ አሜባ የመሳሰሉ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ወደ ሰውነታችሁ ስለሚገቡ ለትኩሳትና ለተቅማጥ ትጋለጣላችሁ፡፡ ተቅማጥ ደግሞ ከሰውነታችሁ ፈሳሽ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ ይህም ለጉዳት፣ በጣም ሲብስም እስከሞት የሚያደርስበት አጋጣሚ አለ፡፡

ሁልጊዜ ከመመገባችሁ በፊት እና በኋላ እንዲሁም የትኛውንም ጨዋታ ተጫውታችሁ ስትጨርሱ እጃችሁን በውሀና በሳሙና በደንብ አሽታችሁ መታጠብ ይኖርባችኋል፡፡ ‘ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንደሚባለው ከሚጎዳችሁ ነገር መራቅ ይኖርባችኋል፡፡ አንድ ጊዜ እነዚህ በሽታ አምጪ ባክቴሪያና ፓራሳይት ወደ ሰውነታችሁ ከገቡ በኋላ ደጋግመው የመመላለሰ ችግር ያጋጥማችኋልና ራሳችሁን መጠበቅ ይገባችኋል፡፡ እንግዲህ ልጆች እጅ መታጠብ ራስን ከበሽታ የሚከላከሉበት ቀላል እና ወሳኝ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ልጆች፤ እጅን መታጠብን ባህል ማሳደግ አለባችሁ፡፡” ሲሉ ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review