የአንዳንድ ሰዎች አካላዊ ሕይወት ቢያበቃም፣ የፈጸሟቸው መልካም ነገሮች፣ ያስመዘገቦቸው ታሪካዊ ድሎች፣ ያበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች ወይም ያስተላለፉቸው መልዕክቶች በሕዝብ ልብ ውስጥ ሕያው ሆነው ይቀጥላሉ። “ስም ከመቃብር በላይ ዋለ” የሚለው አባባል ወይም ምሳሌያዊ አነጋገርም የሚመጣው እዚህ ጋር ይሆናል፡፡ ይህም የሰዎች ተግባር እና ማንነት ከሞት ጋር የማያልፍ ነገር መሆኑን የሚያሳይ ጥልቅ አገላለጽ ነው።
በዚሁ መነጽር የስፖርቱን ዓለም ከተመለከትነው ከሞቱ በኋላም ስምና ተግባራቸው በሕዝብ ዘንድ ሲከበርና ሲወደስ የሚኖር ገዘፍ ያሉ ስብዕና ያላቸው ስፖርተኞ አሉ፡፡ የስፖርት ጀግኖች በሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም ትልልቅ አሻራ ያኖራሉ። በዚህ ጽሑፍም ከሰሞኑ በጃፓን መንገድ በስሙ የተሰየመለትን አትሌት አበበ ቢቂላን መነሻ አድርገን ከህልፈታቸው በኋላ ዓለም ያከበራቸው ስፖርተኞችን በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡
በስማቸው የተሰየሙ መንገዶች፣ ስታዲየሞች እና ሀውልቶች ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት ይሰጣሉ። በቶኪዮ ጎዳናዎች የነገሰው አበበ ቢቂላ ከሮም ኦሎምፒክ በኋላ ያስቀመጠው አሻራ፤ ስፖርት የዘር፣ የቋንቋ እና የሀገር ድንበር እንደሌለው ያሳያል። እነርሱ ባሳዩት ትጋት፣ ቁርጠኝነት እና ችሎታ ምክንያት ስማቸው ለዘላለም ይኖራል። በሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ ስም በጃፓን ካሳማ መንገድ መሰየሙ ይፋ የተደረገው ከሰሞኑን ነበር፡፡
የጃፓን ኦሎምፒክ የማራቶን አሸናፊው ሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ መንገዱ የተሰየመለት በጃፓን ዮኮሃማ እየተካሄደ በሚገኘው ዘጠነኛው የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ልማት ኮንፈረንስ ማጠቃለያ ላይ ነው፡፡ የካሳማ ከተማ ከንቲባ ያማጉቺ ሺንጁ በሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ ስም የተሰየመው መንገድ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ የሚያሳድግ እና ግንኙነት የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኦሎምፒክ ዶት ኮም ገጸ ድር መረጃን በዋቢነት ስንጠቅስ እንደምናገኘው እ.ኤ.አ. በ1960 የሮም ኦሎምፒክን በባዶ እግሩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የመጀመርያውን ወርቅ ያመጣው አትሌት አበበ ቢቂላ እ.ኤ.አ 1964ቱ የቶኪዮ ኦሎምፒክ በድጋሜ ታሪክ የሰራበት ነበር፡፡ በባዶ እግሩ የሮም ኦሎምፒክ ማራቶንን ሲያሸንፍ፣ የራሱን ስም ብቻ ሳይሆን የሀገሩን ኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከፍ አድርጓል። ከዚህ ቀደምም ሻምበል አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ድል ባስመዘገበበት ጣልያን በሮም ከተማ በስሙ በተሰየመ ጎዳና ላይ የእርሱ ምስል ያለበት ማስታወሻ መቀመጡ ይታወሳል።
ልክ እንደ አትሌት አበበ ቢቂላ ሁሉ ከሀገራቸው ውጪ በስማቸው ትላልቅ ስታዲየሞች፣ መንገዶች እና ሀውልቶች የተሰየሙላቸው ስፖርተኞችን ቀጥለን እንመልከት፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ስፖርተኞች መካከል አርጀንቲናዊው ኮከብ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና አንዱ ነው፡፡ ዲያጎ ማራዶና እ.ኤ.አ. የጣሊያን ሊግ (ሴሪ ኤ) እንደ ጁቬንቱስ፣ ኤ.ሲ. ሚላን እና ኢንተር ሚላን ባሉ ጠንካራ የሰሜን ኢጣሊያ ክለቦች የተመሰቃቀለ ነበር። የደቡብ ኢጣሊያ ከተማ የሆነችው ናፖሊም ከኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ጋር ትታገል ነበር።
ተጨዋቹ እ.ኤ.አ. በ1984 ወደ ናፖሊ ሲመጣ የከተማዋን የስፖርት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የማህበራዊ ገጽታዋንም ቀይሯል። በወቅቱ ከባርሴሎና ወደ ናፖሊ ሲዘዋወር ናፖሊ በጣሊያን እግር ኳስ የላቀ ስኬት የሌለው ክለብ ነበር። ናፖሊ በወቅቱ በሰሜናዊ ጣሊያን ከተሞች ከነበሩት እንደ ሚላን እና ቱሪን ካሉ ቡድኖች የሚጠበቅ አልነበረም። ማራዶና ግን ናፖሊን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሴሪያ ኤ ሻምፒዮናነት መርቷታል። ከሞተ በኋላ የከተማዋ ትልቁ ስታዲየም የሆነው ስታዲዮ ሳን ፓኦሎ ስሙ ተቀይሮ ስታዲዮ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና መባሉ፣ ከስፖርት ክብር በላይ የነበረውን ግንኙነት ያሳያል። ይህ ክብር ለናፖሊ ህዝብ ማራዶና ከስፖርት ባሻገር በሕይወታቸው ውስጥ ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደነበረው ያሳያል።
ማራዶና ስታዲየም ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም የከተማዋን እና የደቡብ ጣሊያን ኩራት ከፍ አደረገ። በጣሊያን ሊግ ውስጥ ናፖሊን ወደ ፊት መምራት ደቡብ ጣሊያን በኢኮኖሚ ከበለጸገው ሰሜናዊ ክፍል ጋር እኩል መወዳደር እንደምትችል እንደማሳያ ተቆጠረ። ማራዶና በናፖሊ በቆየባቸው ሰባት ዓመታት (ከ1984-1991) ክለቡን ወደ ታሪካዊ ስኬቶች መምራቱን የዘጋርዲያን ዘገባ ያሳያል። ናፖሊ ለመጀመሪያ ጊዜ የጣሊያንን ሊግ በ1987 አሸንፏል። ይህንን ስኬት እ.ኤ.አ በ1990 ደግሞ በድጋሚ ደግመውታል። ይህ ለከተማዋ የነበረው ትርጉም ከስፖርት ድል ብቻ ሳይሆን የደቡብ እና የሰሜን ጣሊያን የፉክክር ምልክት ሆኖ ይታይ ነበር። በተጨማሪም ሌሎች የአውሮፓ ድሎችን ከአርጀንቲናዊው ኮከብ ጋር አጣጥመዋል።
ቡጢኛው ሙሐመድ አሊ ከቦክስ በላይ የሆነ ስብዕና ነው ይላል ‘The Greatest’: How Muhammad Ali changed the world‘ ዘጋቢ ፊልም፡፡ የእሱ አሻራ ከመቃብር በላይ ለመሆኑ በስፖርቱ ዓለም ካስመዘገበው ስኬት በተጨማሪ በሙስሊሙ ዓለም ለኃይማኖታዊ ማንነቱ የነበረው ጽናት፣ ለሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ የነበረው ትግል በዩናይትድ ኪንግደምና በአሜሪካ ለዘር እኩልነት የሚታገሉ ማህበረሰቦች ዘንድ የነፃነት እና የፍትህ ምልክት አድርጎታል። ለዚህም ነው በዓለም ዙሪያ በበርካታ ከተሞች ያሉ ጎዳናዎች እና ማዕከላት በስሙ የተሰየሙት።
የፍራንስ 24 ቡጢኛውን አስመልክቶ በሰራው ዘጋባ ላይ እንደሚያሳው የዓለማችን ምርጥ ቦክሰኛ በመባል የሚታወቀው ሙሐመድ አሊ፣ በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች በሚገኙ መንገዶች፣ ማዕከላት እና የህዝብ ቦታዎች ስሙ ተሰጥቷቸዋል። በተለይም በዩናይትድ ኪንግደም እና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በስሙ መንገዶች ተሰይመውለታል። አሊ በሲቪል መብቶች እንቅስቃሴዎች ውስጥ የነበረው ተሳትፎና ለእኩልነት ባደረገው ትግል በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በተለይም በጥቁር ማህበረሰቦች ዘንድ ትልቅ አድናቆትን አስገኝቶለታል። በለንደንና በሌሎች ከተሞች ያሉ በርካታ መንገዶች እና ማዕከላት በእሱ ስም መጠራታቸው ለዚህ ማሳያ ነው።
ሙሐመድ አሊ ከቦክሰኛነት ያለፈ ታሪካዊ ሰው በመሆኑ በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ማኅበራትና ሕዝቦች የራሳቸው አድርገው እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል። ይህ ደግሞ በበርካታ ሀገራት የሚሰጡት ክብር እና በእሱ ስም የተሰየሙ ቦታዎች ቁጥር ለምን የበዛ እንደሆነ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
የእግር ኳሱ ንጉስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ብራዚላዊው ፔሌ እንደዚሁ በሀገሩ የበርካታ ስፖርት ማዕከላት እና የስልጠና አካዳሚዎች መስራችና ባለቤት ሲሆን ከብራዚል ውጪ በብዙ ሀገራት ያሉ የኳስ ማዕከላት እና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በስሙ ተሰይመውለታል። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ኪንግደም እና በቻይና በርካታ የስፖርት ማዕከሎችን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል።
በጥቅሉ መንገድ ወይም አውራ ጎዳና በስፖርተኛ ስም መሰየም ትልቅ ክብር ሲሆን ይህንን ክብር የሚያገኙት ደግሞ በስፖርቱ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለዓለም እና ለሰው ልጆች ሁሉ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባት ነው።
በሳህሉ ብርሃኑ