አዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከል እየሆነች ነው – የምጣኔ ሀብት ምሁር ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)

You are currently viewing አዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከል እየሆነች ነው – የምጣኔ ሀብት ምሁር ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)

AMN -ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም

አዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከል እንድትሆን በመንግስት በኩል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከተማዋን ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም ከተማ አስተዳደሩ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየተገበረ ይገኛል። ይህም በመሆኑ መዲናዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ150 በላይ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በአግባቡ አስተናግዳለች።

አዲስ አበባ ከተማ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ 200 ቢሊዮን ብር ተጠቃሚ መሆኗን የከተማዋ ቱሪዝም ኮሚሽን በቅርቡ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በበጀት ዓመቱ ከውጭ ሀገር ቱሪስቶች 143 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ደግሞ 55 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ወደ ከተማው ኢኮኖሚ ፈሰስ መደረጉንም ገልጿል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ በ2017 በጀት ዓመት ከአስር ሚሊየን በላይ የውጭ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከተማዋን ጎብኝተዋል። የምጣኔ ሀብት ምሁር የሆኑት ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል እንግሊዘኛ ጋር ባዳረጉት ቃለ መጠይቅ፤ በአለም ውሰጥ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞች በኮንፈረንስ ቱሪዝም ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)፤ ባንኮክ፣ ዱባይ፣ ኒውዮርክ፣ እና ከአፍሪካ እንደ ጆሃንስበርግ እና ናይሮቢ ያሉ ከተሞችም ትልቁ ገቢያቸው ከኮንፈረንስ ቱሪዝም እና ተያያዥ ከሆኑት የአገልግሎት ዘርፎች ነው ብለዋል። አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗን ዶ/ር ጉቱ ገልፀው፤ የኮንፈረንስ ቱሪዝም በሀገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተፅእኖ እንዳለው በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩ ማህበረሰቦች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ስለማበርከቱም አመላክተዋል ። የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የእደ ጥበብ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ታዋቂው አየር መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ቱሪዝም እና እንግዳ ተቀባይነትን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይጫወታል ሲሉም የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አፅንኦት ሰጥተውበታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዘርፉ ተጠቃሚነቱን ሲገልፁ፣ ላለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ከአፍሪካ እና ከአለም ምርጥ አየር መንገዶች ውስጥ አንዱ ሆኖ መመረጡን ተናግረዋል። ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጎብኝዎች እና ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኝ አስችሎታል ይላሉ። ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) አያይዘውም በእደ ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችም በኮንፈረንስ ቱሪዝሙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚመጡ ቱሪስቶች የቱሪዝም ምርቶችን በመሸጥ ፣ ከዘርፉ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ነው ዶክተር ጉቱ የገለፁት።

ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም አንድ ወይም ሁለት ብቻ አለመሆኑን ተናግረው፣ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ለሕዝብና ለሀገር ብዙ ጥቅም እንዳለው የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አረጋግጠዋል። የኮንፈረንስ ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማደግ ለምግብና መጠጥ፣ ለእንስሳት ተዋጽኦ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ አቅራቢዎች ከፍተኛ ጠቃሚታ አለው። ይህ በመሆኑም በገዢዎች እና ሻጮች መካከል ያለውን የእሴት ሰንሰለት እንደሚጨምረው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተውበታል።

ጉቱ (ዶ/ር) ኮንፈረንስ ቱሪዝም ከማህበራዊና ዲኘሎማሲያዊ ተጠቃሚነት አንፃር ሲናገሩ፤ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርገዋል ብለዋል። ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ ቱሪስቶች ለመጎብኘት የሚጠብቁ ልዩ እና አስደናቂ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሏት ሀገር ናትም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏት ሀገር በመሆኗ፤ የኮንፈረንስ ቱሪዝሙ የእነዚህን ህዝቦች ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ወግ እና ልማድ ለሌላው አለም ለማስተዋወቅ ይጠቅማል ብለዋል የምጣኔ ሀብት ምሁሩ። የኮንፈረንስ ቱሪዝም ጥቅሙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ብቻም ሳይሆን ፣ ለህዝብና ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ዶክተር ጉቱ ተናግረዋል።

በብርሃኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review