ዛሬ ከጠዋቱ 12:40 ሠዓት በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ሳንሱሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሠ የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ14 ሠዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
የጉዞ አቅጣጫውን ከሳንሱሲ ወደ ፒያሳ ያደረገ የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 A 49812 አ/አ የሆነ ሸገር ባስ በቦታው ላይ ከሚገኝ ተርሚናል ተሳፋሪዎችን ጭኖ በሚወጣበት ወቅት በተመሳሳይ አቅጣጫ ጉዞውን ካደረገ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3 A 69183 አ/አ ከሆነ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ጋር ተጋጭተው በወቅቱ ትራንስፖርት በመጠበቅ ላይ የነበሩ 3 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ በ14 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
የመንገድ ትራፊክ አደጋ በየጊዜው የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መንስኤ በመሆን ለከፍተኛ የምጣኔ ሀብትና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እየዳረገ በመሆኑ አሽከርካሪዎችም ሆኑ የመንገድ ተጠቃሚ እግረኞች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አሳስቧል።