ታላቋ ጋዜጠኛና ደራሲ የምወድሽ በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች።
የምወድሽ በቀለ የፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆና ረጅም አመታት አገልግላለች። በድርሰትና በስነ ግጥም ስራዎቿም በርካታ አበርክቶዎች ነበሯት። በ1979 ዓ.ም አብዮታዊ ግጥሞች ከሚለው ስራዋ ጀምሮ ወደ 16 መፃሕፍትንም አሳትማለች። የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያት ማሕበርን በፕሬዝደንትነት ዘለግ ላሉ አመታት መርታለች።
የኢትዮጵያ ሴቶች ማሕበራት የቦርድ ሰብሳሰቢ ሆናም አገልግላለች። ሴቶች ይችላሉ Women can do it የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት መስራችና ዋና ዳይሬክተር ነበረች። እጅግ በርካታ የበጎ ስራ ማሕበራት ውስጥ መስራችና አመራር ሆና ስታገለግል ኖራለች።
በሴቶች፣ በሕፃናት እና ማሕበረሰብ አቀፍ የበጎ ስራዎች ላይ ከፊት ተሰልፋ ሙሉ ጊዜዋን ስትሰራ ቆይታለች። በአሐዱ ሬዲዮ ላይ ከምወድሽ ገፆች የተሰኘ በሴቶች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅም ነበረች። በአሻም ቴሌቪዥን የሚተላለፍም የምወድሽ ገፆች አዘጋጅ ናት። በሕይወት ዘመኗ በርካታ ሽልማቶችንም ባበረከተቻቸው አስተዋፅኦዎች አግኝታለች። የ2016 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ ሌሎችንም አግኝታለች።
ጋዜጠኛ እና ደራሲዋ የምወድሽ በቀለ ከእናቷ ወ/ሮ ወርቅነሽ ወልደማሪያም እና ከአባቷ ሻምበል ባሻ በቀለ ወ/ገብርኤል ነሐሴ 19/1952 ዓ.ም እንደተወለደች የሕይወት ታሪክ ማህደሯ ይገልጻል። አንጋፋዋ ጋዜጠኛ እና ደራሲ የምወድሽ በቀለ ባጋጠማት ሕመም በሕክምና ስትረዳ ቆይታ ነሐሴ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።