የትራፊክ አደጋን 50 በመቶ መቀነስና የተጎጂዎችን ህይወት ለመታደግ የሚያግዝ ፕሮጀክት ተዘጋጀ

You are currently viewing የትራፊክ አደጋን 50 በመቶ መቀነስና የተጎጂዎችን ህይወት ለመታደግ የሚያግዝ ፕሮጀክት ተዘጋጀ

AMN ነሃሴ 24/2017

የተሻሻለው የትራፊክ ህግ ማስከበርና የድሕረ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ የአዲስ አዳማ- ባቱ -ሻሸመኔ የሙከራ ፕሮጀክት ዛሬ ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አባሶ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ ለትራፊክ አደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ህይወት ለመታደግና ለድህረ አደጋ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው። ፕሮጀክቱ የትራፊክ አደጋን 50 በመቶ መቀነስ የሚያስችል እንደሆነ በጥናት እንደተለየ አንስተዋል።

ይህም በሀገራችን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስና የተጎጂዎች ህይወት ለመታደግ ሚና የጎላ ነው ብለዋል። የትራፊክ ደህንነት ለማረጋገጥ በአደረጃጀት፤ አሰራርና ስርዓት በመዘርጋት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ፣ በአማራ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራን እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ለዚህ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ ዘመናዊ አምቡላንሶችና ተሽከርካሪዎች፤ የትራፊክ ደህንነት የሞተር ብስክሌቶች ተዘጋጅቷል ብለዋል። በዚህም የፖሊስ ትራፊክ ፤ ትራንስፖርት ኤጀንሲዎችና የጤና ተቋማት ድሕረ አደጋ የተቀናጀ ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል ።

ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንከ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለአንድ ዓመት የሚቆይ መሆኑን ያወሱት የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ ለውጤታማነቱ በየደረጃው የሚገኘው ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።

የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ ምክትል ሃላፊ አቶ ሌቺሳ ሃዩ በበኩላቸው፤ የአዲስ አዳማ -ባቱ -ሻሸመኔ የትራንስፖርት ኮሪደር የትራፊክ ፍሰት የሚበዛበትና አደጋዎች ደጋግመው የሚከሰቱበት ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ሆስፒታሎች ፤ የፖሊስና ትራንስፖርት ኤጃንሲዎችን በማስተሳሰር በክልሉ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ አኳያ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይ በተጎጂዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስና ህይወት ለመታደግም እንዲሁ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review