የኢትዮጵያን ይግዙ መርህ የሀገርን ኢኮኖሚ በጠንካር መሰረት ላይ ለማኖር የተጀመረውን የኢኮኖሚ ሪፎርም የሚያረጋግጥ መሆኑን ፕሬዝዳት ታዬ አፅቀሥላሴ ገልፀዋል፡፡
2ኛው ሀገር አቀፍ “የኢትዮጵያን ይግዙ” የንግድ ሳምንት ኤክስፖ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ካሳሁን ጎፌ በተገኙበት ተከፍቷል።
የኢትዮጵያ ይግዙ መርህ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እና የውጭ የኢኮኖሚ ተጋላጭነትን በመቀነስ የሀገርን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ለማኖር የተጀመረውን የኢኮኖሚ ሪፎርም የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ተናግረዋል።
በርካታ የአለም ሀገራት የሀገርውስጥ አምራቾችን በማበረታታት፣ በመደገፍና ዜጎቻቸው ምርቶችን እንዲጠቀሙ በማድረግ የዜጎቻቸውን ህይወት ከመለወጥም ባሻገር አለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ ማድረግ የመቻላቸውን ተሞክሮ በመቅሰምም፤ ኢትዮጵያም ይህንኑ ዘርፍ እንድትቀላቀል ዜጎቿ ምርቶቿን መግዛትና መጠቀም ብሎም ለተቀረው አለም ማስተዋወቅ የዜግነት ግዴታቸው ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ምርትን መግዛት አምራቹን ከማበረታታትም ባሻገር የሀገር ውስጥ ኢንደስትሪዎች እንዲነቃቁ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን የመፍጠር ተግባርን የሚያግዝ ስለመሆኑም ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ አክለዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎንፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኤክስፖው የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎት ከማስተዋወቅና ከማበራታታት በተጨማሪ የንግድ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
ኤክስፖው ማህበረሰቡ የሀገሩን ምርት በአንድ ማእከል እንዲያገኝ፤ ብሎም ለሀገር ውስጥ ምርት ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ የሚያስችል ስለመሆኑም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ምርትን የማስተዋወቅ ብሎም የገበያ ትስስርን መፍጠር ሌላኛው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተግባር መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ 2ተኛው የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንትም የዚሁ አንዱ አካል መሆኑን አንስተዋል፡፡
በኤክስፖው ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ ከሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ 168 የንግድ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ የልምድ ልውውጥ መድረኮችም እንደሚደረጉ ተመላክቷል፡፡
በራሄል አበበ