ሠራዊቱ የአገር ሉአላዊነትና ዘላቂ ሰላምን በአስተማማኝ መልኩ የመጠበቅ ተልዕኮውን አጠናክሮ መቀጠሉን ሌተናል ጀነራል ሃጫሉ ሸለመ ገለጹ

You are currently viewing ሠራዊቱ የአገር ሉአላዊነትና ዘላቂ ሰላምን በአስተማማኝ መልኩ የመጠበቅ ተልዕኮውን አጠናክሮ መቀጠሉን ሌተናል ጀነራል ሃጫሉ ሸለመ ገለጹ

AMN ነሐሴ 24/2017

ሠራዊቱ የአገር ሉአላዊነትና ዘላቂ ሰላምን በአስተማማኝ መልኩ የመጠበቅ ተልዕኮውን አጠናክሮ መቀጠሉን በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰው ሃብት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ሃጫሉ ሸለመ ተናገሩ።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዛሬ ለ10ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ምልምል ወታደሮች አስመርቋል።

በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ምልምል ወታደሮቹን ያስመረቁት የዕለቱ የክብር እንግዳና የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰው ሃብት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ሃጫሉ ሸለመ ናቸው።

ሌተናል ጀነራል ሃጫሉ ሸለመ፤ የአገር መከላከያ ሠራዊታችን የአገርን ሉአላዊነትና ዘላቂ ሰላምን በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ተልዕኮውን በስኬት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል ።

ከሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተገመደው የአገር መከላከያ ሠራዊት በሁሉም የግዳጅ ውሎው ድል አድራጊነቱን አጠናክሮ መቀጠሉንም አመልክተዋል።

በውጭ ጠላቶች ተደግፈው የአገሪቱን ሰላም በማደፍረስ በኃይል ስልጣንን ለመቆጣጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት የተከተሉት የተሳሳተ መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዳላዋጣቸውና ወደሰላም መምጣት የጀመሩ እንዳሉም ተናግረዋል።

እንደ ሌተናል ጀነራል ሃጫሉ ገለፃ ሠራዊቱ ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጭም ጠላት የሚከላከልና የሚጠበቅ ተመራጭ የሰላም ኃይል ነው ።

የዛሬ ተመራቂዎችም ይሄን በመረዳት በቀሰሙት ወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎት ታግዘው የአገራቸውን ሉአላዊነት፣ ሰላምና ደህንነት ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች በጀግንነትና በቁርጠኝነት በመጠበቅ አርአያ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ በበኩላቸው፥ የ10ኛ ዙር ተመራቂዎች በቆይታቸው የትኛውንም አገራዊ ግዳጅና ተልዕኮ በታላቅ ጀግንነት መወጣት የሚያስችላቸውን የወታደራዊ ሳይንስ ዕውቀት በተግባርና በንድፍ መቅሰማቸውን ገልጸዋል።

የውትድርና ሙያ ራሳቸውን ለአገርና ለህዝብ አሳልፈው ከሚሰጡና ፍቃደኛ ከሆኑ ዜጎች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደ እዚህ ታላቅ ተቋም የተቀላቀሉትን ተተኪዎች ማመስገናቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለዛሬው የምረቃ መርሃግብር መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት እና በስልጠና ወቅት የላቀ ሥራ ላከናወኑ ክፍሎች ሽልማት ተበርክቷል።

የተዘጋጀውን ሽልማት ያበረከቱት ሌተናል ጀነራል ሃጫሉ ሸለመ እና በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ዋና ኃላፊ ሜጀር ጀነራል አዳምነህ መንግስቴ ናቸው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review