ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ባለመግባባታችን ከታናናሾቻችን በታች ሆነናል ሲሉ ዋና ኮሚሽር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ባለመግባባታችን ከታናናሾቻችን በታች ሆነናል ሲሉ ዋና ኮሚሽር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) ገለጹ

AMN ነሀሴ 24/2017

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሰሜን አሜሪካና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ በዋሺንግተን ዲሲ ዋተር ጌት ሆቴል ተጀምሯል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት ዋና ኮሚሽር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) “እናንተ የምትኖሩባት አሜሪካ በእድሜ ከኢትዮጵያ ያነሰች ብትሆንም በዴሞክራሲ ቁንጮ ላይ ደርሳለች” በማለት ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ ግጭቶችና አለመግባባቶችን ስታሳልፍ በመቆየቷ ለዚህ ደረጃ ለመድረስ አልታደለችም በማለት በንፅፅር አቅርበዋል፡፡

አሁን ግን “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲሉ የማንግባባቸውን እጅግ መሰረታዊ ምክንያቶች በህዝባዊ ውይይት በመለየት ወደ ዘላቂ ሰላም ለመሸጋገር በጉዞ ላይ ነን ሲሉም አክለዋል፡፡

ይህንን ጉዞ ለማሳካት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የካቲት /2014 ዓ.ም ተቋቁሞ ባለፉት አመታት በርካታ ስራዎችን መስራቱን አንስተዋል፡፡

ይህ ሂደት ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ቅደመ ሁኔታና ልዩነት እየተሳተፉበት የሚገኙ ታሪካዊ ሂደት መሆኑንም ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ምክንያቶች ቢሰደዱም የሀገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል በሚል በተለያዩ አማራጮች በምክክሩ ሂደት ለማሳተፍ ኮሚሽኑ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አንዳንዶች ይህንን የኮሚሽኑን እንቅስቃሴ ለመግታት ቢንቀሳቀሱም ብዙዎች ግን ከኮሚሽ ጎን በመሆናቸው ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፤ ለዚህም ይህ በአሜሪካ እየተካሄደው ያለው መድረክ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በዴሞክራሲ ቁንጮ ላይ በምትገኝ ሀገር እየኖሩ መርህ አልባ የሆነ ተቃውሞ የሚጠበቅ አይደለም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ሂደቱን መደግፍ ባይቻል በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጓዝ ግን የተሻለው አካሄድ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ኮሚሽኑ በቀጣይ በካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድንና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአካል ተገኝቶ ተመሳሳይ መድረክ እንደሚያከናውንም ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ የቀሩት ስራዎች ጥቂት ቢሆኑም እጅግ መሰረታዊ የሚባሉ ናቸው ያሉት ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ(ፕሮፌሰር) በቀጣይ የትግራይ ክልል ምክክር መድረክ ማከናወን፣ የዳያስፖራውን መድረክ ማጠናቀቅ እንዲሁም አጀንዳ መቅረፅና ዋናውን ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ አፈፃፀሙን መከታተል ዋና ዋና ተግባራቶች መሆናቸውን ማንሳታቸዉን ኮሚሽኑ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review