ሊቨርፑል ከ አርሰናል በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከሚናፈቁ የእርስ በእርስ ግጥሚያዎች አንዱ ነው፡፡
ሁለቱ የሊጉ ሃያላን ሲገናኙ ግቦች ፣ ድራማዎች ፣ የበረታ የፉክክር መንፈስ እና የላቀ ጨዋታ ስለሚያሳዩ ጨዋታቸው ይናፈቃል። ክለቦቹ የ2025/26 የውድድር ዓመት ገና ጡዘቱ ላይ ሳይደርስ በሦስተኛ ሳምንት ተገናኝተዋል፡፡ ሁለቱም ክለቦች የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታቸውን አሸንፈው ይገናኛሉ፡፡
ሊጉን ለ20ኛ ጊዜ ያሸነፈው ሊቨርፑል ቦርንማውዝን እና ኒውካስትልን ፤ አርሰናል በበኩሉ ማንችስተር ዩናይትድ እና ሊድስ ዩናይትድን መርታት ችለዋል፡፡ ሊቨርፑል በሁለቱ ጨዋታዎች አራት ግብ ሲቆጠርበት ፤ በአርሰናል በኩል ዴቪድ ራያን አልፎ ከመረብ ጋር የተገኛኘ ኳስ የለም፡፡
የሊቨርፑል ደካማ ጎን ተከላካይ ክፍሉ ሲሆን ፤ የአርሰናል ጠንካራ ጎን ደግሞ የመከላከል መዋቅሩ ነው፡፡ አርሰናል በመጀመሪያው ጨዋታ በማንችስተር ዩናይትድ 22 ሙከራ ቢደረግበትም የሙከራዎቹን ጥራት ቀንሷል፡፡ ዩናይትድ ካደረገው 22 ሙከራ በኤክስ ጂ(XG) መለኪያ እንዲያስቆጥር ይጠበቅ የነበረው 1.5 ግብ ብቻ ነው፡፡
ሙከራዎቹ ይብዙ እንጂ የአርሰናል ተከላካዮች ዩናይትድ ግልፅ የማግባት እድል እንዳያገኝ ጥሩ ስራ ሰርተዋል፡፡ ሊቨርፑል በአንፃሩ ባለፉት ዓመታት ድንቅነቱን ያስመሰከረው ቨርጅል ቫንዳይክን ቢይዙም ወደ ግብ የሚሞከር ኳስ ሁሉ የሚገባበት ቡድን መስሏል፡፡ ሁለቱን የሊግ ጨዋታ ሲያሸንፍ 2ለ0 መርቶ 2 አቻ ከሆነ በኋላ ነው ግቦችን አስቆጥሮ ያሸነፈው፡፡
በተለይ የኒውካስትልን በሃይል የታጀበ የጨዋታ መንገድ መቋቋም ተስኗቸው ታይተዋል፡፡ አርሰናል ልክ እንደ ኒውካስትል ሃይልን ቀላቅሎ መጫወት የሚችል ፤ የቆሙ ኳሶችን በመጠቀምም ስሙ በቀዳሚነት የሚጠራ ክለብ ነው፡፡ በአንፊልድ ይህን ብቃት የመድገም እድል ካገኘ ሊቨርፑል አደጋ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ አርሰናል በዚህ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት ይወጣል ብሎ ለመገመት ከባድ ነው፡፡
ሊቨርፑል በአርነ ስሎት እየተመራ ካደረጋቸው 40 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በ39ኙ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ብቸኛ ግብ ያላስቆጠሩበት ጨዋታ በኖቲንግሃም ፎረስት 1ለ0 የተሸነፉበት ነበር፡፡ ቀዮቹ በ39ኙ ጨዋታዎች 93 ግብ ከመረብ አሳርፈዋል ፤ ይህም 2ኛ ላይ ከሚከተላቸው በ17 የላቀ ነው፡፡
አርሰናል ፈታኝ ወደሆነው አንፊልድ ስታዲየም ቢያመራም ከሊቨርፑል ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አልገጠመውም፡፡ ሁለቱን አሸንፎ በአራቱ አቻ ተለያይቷል፡፡ ይሁን እንጂ አርሰናል በአንፊልድ ካሸነፈ 13 ዓመታት አልፈዋል፡፡ መድፈኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ በ2012 ሊቨርፑልን 2ለ0 ሲረቱ ሚካኤል አርቴታ የመሀል ሜዳው መሪ ነበር፡፡
ሊቨርፑል ከ አርሰናል በሊጉ ታሪክ ሁለተኛ በርካታ ግብ የሚቆጠርበት የእርስ በእርስ ግጥሚያ ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች ፕሪምየር ሊጉ እኤአ 1992 በአዲስ መልክ ከተዋቀረ በኋላ ግንኙነታቸው 198 ግቦችን አስመልክቷል፡፡ ዛሬስ? ምሽት 12፡30 በአንፊልድ በዋና ዳኛው ክሪስ ካቫናህ ፊሽካ የሚጀምረው ጨዋታ ምላሽ ይሰጠናል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ