የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያዘጋጀው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ አየር ንብረት ለውጥ ሳምንት ከነሐሴ 26 እስከ ጳጉሜን 1 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ እንደሚደረግ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፤ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ከግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን የጉባኤውን ዝግጅት በማስመልከት ለጋዜጠኞች ያዘጋጀው የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠና ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄዷል።
ከጉባኤው አስቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት (UNFCC) ያዘጋጀው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት ከነሐሴ 26 እስከ ጳጉሜን 1 2017 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል።
ሳምንቱ “ውይይቶችን ወደ ተግባር እና ውጤት መቀየር” በሚል ዋና ሀሳብ የሚከናወን ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ቃል ኪዳኖችን ወደ ሚጨበጥ የተግባር ውጤት መቀየር ላይ ያተኮረ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትና ስትራቴጂክ አጋርነት መሪ ስራ አስፈፃሚ መንሱር ደሴ በአየር ንብረት ለውጥ ሳምንቱ 1 ሺህ 500 ገደማ ልዑክ እንደሚሳተፍ ገልጸዋል።
በሳምንቱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ችግኝ ዋንኛ ሰለባ ናቸው ከሚለው የቆየ ትርክት በመውጣት አህጉሪቷ ለጉዳዩ መፍትሄ አፍላቂ የሆኑ የተግባር ምላሾችን እየሰጠች መሆኑ የሚታይበት ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ሳምንቱ የሀገራት ትልሞች እና የፖለቲካ ቁርጠኝነቶች ወደ ተጨበጠ ለውጥ እንዲቀየር ጠንካራ ጥሪ የሚቀርብበት ነው ብለዋል።
ሳምንቱ ለሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የሚሆኑ የፖሊሲ ሀሳቦችን የሚመመግብና በብራዚል ቤለም ለሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) የጋራ አጀንዳን ለመቅረጽ እንደሚያግዝ አክለዋል።
በሁለተኛው የአየር ንብረት ሳምንት የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ወጣቶች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች እና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ።
በሳምንቱ የከፍተኛ ደረጃ ምክክሮች፣ የጎንዮሽ ውይይቶች፣ የልምድ ልውውጦች፣ አውደ ርዕዮች እና የትስስር ማጠናከሪያ መድረኮች እንደሚከናወኑ ኢዜአ ዘግቧል።
ሳምንቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያካሂደው የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት ሁነቶች አካል ነው።
የሳምንቱ ሁነት አላማ የአየር ንብረት ለውጥ ቃል ኪዳኖች ወደ ተግባር እንዲለወጡ ንቅናቄ ለመፍጠር እና ቀጣይ ለሚደረጉ ሁነቶች አጀንዳ መቅረጫ መድረክ ሆኖ ማገልገል መሆኑን ተመድ አስታውቋል።