የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው

AMN- ነሐሴ 25/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ ገንቢ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአሰራር ዓለም በምትጓዝበት ፍጥነት ራሱን እያበቃ መምጣቱ ይታወቃል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ባሉት ከ340 በላይ ዓለም አቀፍ የወደብ መዳረሻዎች ከየትኛውም የዓለም ክፍል ጭነቶችን ወደ ተፈለገው የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች በባህር እና በየብስ የተቀናጀ የመልቲ ሞዳል የትራንስፖርት ስርዓትን በመጠቀም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና የተሟላ የሎጅስቲክስ አገልግሎትን በመስጠት በገቢ እና ወጪ ንግድ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑም ይታወቃል።

የባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፣ ተቋሙ በወጭ እና ገቢ ንግድ ላይ የየብስ እና የባህር ላይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

እንዲሁም ትልልቅ የመንግስት ፕሮጀክቶች እቃዎችን በማጓጓዝ ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህም ሪፎርም እና መዋቅራዊ ለውጥ በማድረግ አገልግሎቱን በጉልህ ማሳደጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መርከቦች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ኢትዮጵያን እያስተዋወቁ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለው አካዳሚም በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሙያዎች በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን አመላክተዋል።

ዘርፉ እንደ ግብርና፣ ከተማ ልማት፣ ማኑፋክቸሪንግ እና መሰረተ ልማት ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዓመታዊ ገቢ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ወጭ እና ገቢን በማሳለጥ ጊዜ ቆጣቢ የሆነ አገልግሎት በመስጠት በኢኮኖሚ እድገት ጉዞ ውስጥ ገንቢ ሚናን እየተጫወተ እንደሆነ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review