ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀመሩ

You are currently viewing ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀመሩ

AMN- ነሐሴ 25/2017 ዓ/ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

የቦረና ዞን፣ የያቤሎ ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦረና ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ሥፍራ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዘመናት የገዳን ሥርዓት ጠብቆ ያቆየ፣ የሀገሩን ድንበር ሲጠብቅ የኖረ ሕዝብ ነው ብለዋል።

የቦረና ሕዝብ ኤልሶድ (ጨው ቤት) ከሚባለው ሥፍራ ጨው እያመረተ ለኢትዮጵያውያን ሲመግበን ኖሯል፤ ለዚህም እናመሰግናለን ነው ያሉት።

በድርቅ ሲፈተን የነበረው ቦረና ያ ሁሉ አልፎ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በሚያስችል መንገድ ላይ ነን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችን ድርቅና ረሃብን የትናንት እንጂ የዛሬና ነገ ታሪካችን አካል አይሆኑም ብለዋል።

የቦረና ሕዝብ ለዘመናት የዘለቀ የውኃ አጠባበቅና አቀማመጥ ባህል እንዳለው አንስተዋል።

መንግሥት በሁሉም አካባቢ ፈጣን ልማትና እድገትን ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርትን ማስፋፋትም ልማትን ለማፋጠን ጉልህ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

ዛሬ ሥራ የጀመረው የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያም የመንግስት ፖሊሲ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ መገንባት የቦረና ዞን ህዝብ የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄን የመለሰ፣ የአካባቢውን እምቅ የልማት ፀጋ ለመጠቀም ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ይህ አውሮፕላን ማረፊያ የቦረናን ባህል፣ ታሪክ፣ የገዳ ሥርዓት፣ የያቤሎን የአዕዋፍ መናኸሪያ፣ የቦረናን ፓርክ ለማየትና ለማድነቅ ዕድል ይሰጣል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያንና አፍሪካን ከመላው ዓለም ጋር የሚያገናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁሉም አቅጣጫ የሚኖሩትን የሀገራችን ህዝቦች እርስ በርስ በአየር በማገናኘት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር ከፍተኛ ሚና በመወጣት ላይ ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የበለጠ እንዲያስፋፋ እና እንዲያዘምን መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review