ህንድ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከሌሎች የመካከለኛው፣ ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ እስያ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መሪዎች ጋር በመሆን የሻንጋይ የትብብር ድርጅት የሁለት ቀናት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ቻይና ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉበኤውን ለመካፈል ቻይና የገቡት ከ7 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ናሬንድራ ሞዲ እና ሺ ጂን ፒንግ ባደረጉት ቁልፍ ስብሰባም፣ ለዓመታት የዘለቀ ከድንበር ጋር የተያያዘ ልየነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኤክስ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክትም፣ ህንድ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት በመከባበር፣ በመተማመን እና ባለመጎዳዳት ላይ በተመሰረተ መልኩ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የሁለትዮሽ ስብሰባው የተካሄደው ህንድ የሩሲያን ነዳጅ ትገዛለች በሚል አሜሪካ የ50 በመቶ ታሪፍ ከጣለችባት ከአምስት ቀናት በኋላ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በታምራት ቢሻው