የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ከፍታውንና የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ

You are currently viewing የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ከፍታውንና የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ

AMN – ነሐሴ 25/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ከፍታውንና የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1 ቢሊየን ብር ወጪ ያስገነባውን የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ አስመርቆ አገልግሎት አስጀምሯል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ አየር መንገዱ ወደ ያቤሎ በረራ መጀመሩ ለተቋሙ፣ ለያቤሎና አካባቢው ህዝብ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።

በአካባቢው አዳዲስ የንግድ፣ የጉብኝትና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንደሚከፍትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዘመናት በሚታወቅበት ከፍታ ለመቀጠል በሦስት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሀገር ለአፍሪካና ለሌላው ዓለም ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሀገራችንን ወጣቶች በአቪዬሽን እያሰለጠንን እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል።

ሁለተኛ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማስፋፋት መሆኑን ጠቅሰው፣ በሦስተኛ ደረጃ አውሮፕላኖቻችን እያዘመንን የአውሮፕላኖቻችንን ቁጥር እያሳደግን እንቀጥላለን ብለዋል።

አየር መንገዱ በያቤሎ በሳምንት ሦስት ጊዜ የበረራ አገልግሎት በመስጠት የሀገር ውስጥ የበረራ አድማሱን ማስፋቱን ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱ በቀጣይ ከሀገር ውስጥ መዳረሻ ማስፋት ባለፈ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን አስጠብቆ ለመቀጠል በቢሾፍቱ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ አየር መንገዱ ወደ ያቤሎ የጀመረው በረራ ትልቅ የልማት አንቀሳቃሽ፣ የህዝብ ትስስርን የሚያጠናክር፣ ንግድን የሚያስፋፋ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ለሀገር ውስጥ በረራ ከ30 በላይ አውሮፕላኖችን በመመደብ በበርካታ ከተሞች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግንባታቸው ከተጀመሩ ስድስት አውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል በ2016 አገልግሎት የጀመረው የነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያና ዛሬ አገልግሎት የጀመረው የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያን ጠቅሰዋል።

የነገሌ ቦረና፣ ጎሬ መቱ፣ ሚዛን አማንና ደብረማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ በ2018 ተጠናቀው አገልግሎት እንደሚጀምሩ አንስተዋል።

በቀጣይም የአዳዲስ የመንገደኞች ማስተናገጃና ነባሮችን የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተነገሩት ።

የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በ1 ቢሊየን ብር ወጪ በአራት ዓመት መጠናቀቁን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review