ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያዘጋጀው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 1 /2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ይጠበቃል፡፡ ሳምንቱ “ውይይቶችን ወደ ተግባር እና ውጤት መቀየር” በሚል ዋና ሀሳብ የሚከናወን ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ቃል ኪዳኖችን ወደ የሚጨበጥ የተግባር ውጤት መቀየር ላይ ያተኮረ ነው።
አፍሪካ ከቃል ኪዳኖች ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅ ሀገር በቀል መፍትሄዎችን እየተገበረች መሆኑም ተመላክቷል። የአየር ንብረት ሳምንቱ የሀገራት ትልሞች እና የፖለቲካ ቁርጠኝነቶች ወደተጨበጠ ለውጥ እንዲቀየሩ ጠንካራ ጥሪ የሚቀርብበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ሳምንቱ ለሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የሚሆኑ የፖሊሲ ሀሳቦችን የሚመግብና በብራዚል ቤለም ለሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) የጋራ አጀንዳን ለመቅረጽ እንደሚያግዝም ይጠበቃል።
በሁለተኛው የአየር ንብረት ሳምንት የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ወጣቶች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች እና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ፡፡ የ2025 የመጀመሪያ የአየር ንብረት ሳምንት (CW1) እ.ኤ.አ በግንቦት ወር 2025 በፓናማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
በተመስገን ይመር