በመዲናዋ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸዉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing በመዲናዋ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸዉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN ነሐሴ 26/2017

በአዲስ አበባ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 32ኛውን ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ጉባዔው “በዕውቀት እና በክህሎት ትውልድን በማፍራት ኢትዮጵያን ተምሳሌት አገር እናደርጋለን” በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ በዕውቀት እና በክህሎት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ለትምህርት ጥራት አጋዥ የሆኑና የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን የሚስችሉ ተግባራት በማከናወን ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

በዚህም በእውቀትና በአካል የዳበረ ትውልድ ለማፍራት፣ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ለመስጠት መቻሉን ገልጸዋል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትምህርት ቤቶችን የማዳስ፣ የመገንባት እና ምቹ የሆነ የመማር ማስተማር ሁኔታ መፍጠር ፣ የትምህርት ቤት ምገባ እና ሌሎች ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

ትምህርት ለአገር እድገትና ብልጽግና መሰረት መሆኑን ተከትሎ ለትምህርት ጥራት ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀው በተለይም በቅድመ መደበኛ ትምህርት የነገ ትውልድን ለመገንባት ያስቻሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ትኩረት ለትምህርት ዘርፉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

በቀጣይ በ2018 ዓም ውጤታማ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንዲኖር የባለድርሻ አካላት ቅንጅት የበለጠ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል። ከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ እንዲሆኑ እና ከአዋኪ ድርጊቶች እንዲጸዱ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እና የቁሳቁስ አቅርቦት መካሄዱ ተማሪዎች በስፋት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ማስቻሉን ጠቅሰዋል። በአዕምሮ፣ በአካል የዳበረ ጤናማ ትውልድ ለማፍራት የሚያግዙ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ውድድሮች መካሄዳቸውንም አስታውሰዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review