ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ባከናወናቸው ተግባራት ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ አስታወቁ።
አቶ አደም ፋራህ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የዳካ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
አቶ አደም በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት አመታት የህዝቡንና የሀገሩቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ተግባራት ስኬታማ ናቸው። ለስኬቱም መላው አባላቱና ደጋፊዎቹ የመደመር ፍልስፍናን ተከትለው መስራት በመቻላቸውና ለፓርቲው በትጋት በማገልገል እንደሆነ ተናግረዋል።
የሲዳማ ህዝብ ለፓርቲው ባለው ዕምነትና ታማኝነት የሚወርዱ አቅጣጫዎችን በመቀበል በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ባደረገው ተሳትፎ በግንባር ቀደምነት በመስራት ለሌሎች ምሳሌ መሆን እንደቻለም ገልጸዋል። በሌሎች የልማት ስራዎች በንቃት በመሳተፍ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በኮሪደር ልማት ስራ ሀዋሳ ባላት ውበት ላይ ተጨማሪ ውበት ያላበሰ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ህዝቡ ለክልሉ ልማት በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀት የሚጠበቅበትን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ፓርቲው የተመቸ ተቋም እንዲኖረው የአባላቱና የደጋፊዎቹን አቅም በመጠቀም ምቹ ጽህፈት ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱንም ተናግረዋል።
የፓርቲው የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ እንዳሉት የተገነባው ባለ አራት ወለል ህንጻ ለስራው ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው። በክልሉ ተግባራዊ በተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በርካቶች እንደተለወጡም ገልጸዋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለሰ ዓለሙን ጨምሮ ሌሎች የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ።