ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በፈጠረው ሀይቅ ከሚያመርቱት ዓሣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንጌ ወረዳ ወጣቶች ተናገሩ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በፈጠረው ሀይቅ የዓሣ ምርት ተጠቃሚ ከሆኑት አካባቢዎች መካከል በአሶሳ ዞን የሸርቆሌና እና መንጌ ወረዳዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በመንጌ ወረዳ ፍርዶስ ቀበሌ ወጣቶች በማሕበር ተደራጅተው ግድቡ ከፈጠረው ሀይቅ የዓሣ ምርት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸወን ኢዜአ ዘግቧል። ከተጠቃሚዎቹ ውስጥ ወጣት ሚካኤል አነጁም እንደተናገረው፤ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓሣን በማምረት በኑሯቸው ይበልጥ እንዲሻሽሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
ከዓሣ ምርት ሽያጭ ከሚያገኙት ገቢ ለዓፃ ምርት ማጓጓዣ ሞተር ብስክሌት እና ፍሪጅ በመግዛት ጭምር ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እያሳደጉ መሆኑን ተናግሯል። ወጣት ረመዳን ሰኢድ በበኩሉ፤ ግድቡ በፈጠረላቸው መልካም አጋጣሚ በየቀኑ ዓሣ በማስገር ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል።
ግድቡ የፈጠረላቸው ሀይቅ ለዓሳ እርባታ ምቹ በመሆን ዓሣ በማስገር የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል ያሉት ደግሞ ወጣት ኢብራሂም አለሚን ነው።
በቀጣይም ይበልጥ ምርት ማግኘት የሚያስችላቸው መደላድል መፈጠሩን ጠቁሞ፤ ምርቱን በፍጥነት ለገበያ ለማድረስ በአካባቢው የተጀመረው የመንገድ መሠረተ ልማትም ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርላቸው ጠቅሷል። የወረዳው ነዋሪ ሀሊፋ ሙሐመድ በበኩሉ፤ ከዓሣ ምርት በተጨማሪ ባሕላዊ ጀልባዎችን በአካባቢው በመስራት ወደ ስራ እየገቡ መሆናቸውን ነው የተናገረው።
የመንጌ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ሙሳ፤ የሕዳሴ ግድብ ትሩፋት የሆነው የዓሣ ምርት በወረዳው እየተመረተ ነው ብለዋል። በወረዳው በማሕበር ተደራጅተው በዓሣ ምርት የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ እንዲሆኑም የጀኔሬተር እና የምርት መሸጫ ቦታ መመቻቸቱን ገልጸዋል።