ህዳሴን የመገንባት ሂደቱ እጅግ አታካች፣ አድካሚ፣ አሰልቺ እና አጨቃጫቂ ቢሆንም ፍሬው ግን እጅግ በጣም ጣፋጭ ነዉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መላዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ጨምሮ በፕሮጅክቱ የግንባታ ሂደት ዉስጥ የደምና የላብ ጠብታ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያዊያ አባይን ጨምሮ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ሃገር ብትሆንም ያለንን ጸጋ በትኩረት ማየት ባለመቻላችን የድህነት ምሳሌ ሆነን እንድንቆይ አድርጎናል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከበርካታ ውስብስብ ችግሮች ተላቆ ለፍፃሜ መብቃቱ ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ድል ነዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አባይ ዉሃችንን ብቻ ሳይሆን አፈራችንን እና ወርቃችንን ጭምር አጥቦ ሲሄድ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከበርካታ ዉጣ ዉረዶችና ዉስብስብ ችግሮች በኋላ ፕሮጀክቱ ለምረቃ መብቃቱን አንስተዋል፡፡
የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ ስንጀምር የገንዘብ ድጋፍም ሆነ ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ሀገር የለም ፤ ይሁን እንጂ ግድቡን በራሳችን አቅም ገንብተን ማጠናቀቅ ከውሃ ውስጥ ብርሃን ማውጣት ችለናል ብለዋል፡፡
ታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ጨለማ ለወረሳቸው እና በድህነት ውስጥ ላሉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ብርሃን ፈንጥቆላቸዋል ፤ይህ ለእኛ ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ ሂደት እጅግ አታካች፣ አድካሚ፣ አሰልቺ እና አጨቃጫቂ ቢሆንም ፍሬው ግን እጅግ በጣም ጣፋጭ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በአስማረ መኮንን