ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በቀጣይ ሳምንታት ለጎብኝዎች ክፍት እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ

You are currently viewing ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በቀጣይ ሳምንታት ለጎብኝዎች ክፍት እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ

‎AMN ነሀሴ 26 /2017 ዓ.ም

‎የኢትዮጰያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በቀጣይ ሳምንታት ዉስጥ ለጎብኝዎች ክፍት እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን ያስታወቁት የህዳሴ ግድብ በተገነባበት ጉባ ላይ ከማህበራዊ ጉዳይ አማካሪያቸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በገለጻቸው፤ በዘንድሮ ዓመት ሀምሌና ነሃሴ ወራት ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ የመጡ የዳያስፖራ ጎብኝዎች ፍሰት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር በሃምሳ በመቶ መጨመሩን ጠቅሰው፤ ይህ በዘርፉ ከፍተኛ ገቢ እንዲገኝ ማስቻሉን አብራርተዋል።

‎ታላቁ የህዳሴ ግድብ ደግሞ የኢትዮጵያን ማንሰራራት በተጨባጭ ከማብሰሩም ባሻገር ለቱሪዝም ፍሰት ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል።

‎ለኛ ይበልጥ ጉልበት የሚሰጠን ማየት ያልቻሉት መጥተው ግድቡን ሲያዩት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት የህዳሴ ግድብ ለመላው ኢትዮጰያውያን ለጉብኝት ክፍት ይደረጋል ብለዋል።

‎‎ለዚሁ ስራ የሚሆን አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም አንስተዋል።

‎የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥ ዝግጅት ማጠናቀቁንና በግድቡ ከመቶ የሚበልጡ ዘመናዊ የማረፊያ ቪላዎች መዘጋጀታቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

‎ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የዘመናት ፈተና በመተባበር ክንድ እንዴት ማስቀረት እንደተቻለ ትምህርት የሚሰጥ ስለመሆኑ አንስተው፤ ጎብኝዎችም ከዚህ ብዙ ትምህርት እንደሚወስዱ ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።

‎የግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለግድቡ ግንባታ ሂደት አስተዋጽኦ ላበረከቱት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review