በእያንዳንዷ ቀን ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ጉዳይ ጀምራ እየጨረሰች የኢኮኖሚ ቦታዋን ታሻሽላለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ለሺህ ዓመታት ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ሆኖ የቆየውን ዓባይን ፈትተናል፤ ካሁን በኋላ ያለው የዓባይ ውላጅ ስለሆነ ቀላል ነው ሲሉም ገልጸዋል። “የኩስመና ታሪክ ማብቂያ” በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት የጉባ ላይ ወግ፤ የሕዳሴው ግድብ በተሟላ ሁኔታ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲክስ ኩስመና ታሪክ አብቅቷል ብለዋል።
ለሺህ ዓመታት ለኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና ዓባይ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌላው የዓባይ ውላጅ ነው፤ ትልቁን ፈተና ፈትተናል፤ ሌላው ቀላል ነው ሲሉም አብራርተዋል። ጀምረን መጨረስ እንደምንችል በሕዳሴው ግድብ አይተናል፤ በቀጣዮቹ አምስት፣ አሥር እና 15 ዓመታትም እንደ ሕዳሴ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንጀምራለን፤ እነዚህ ሥራዎችም የኢኮኖሚ ስፍራችንን ያስተካክላሉ ብለዋል።
ምንም ጥርጥር የለውም በእያንዳንዷ ቀን ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ጉዳይ ጀምራ እየጨረሰች የኢኮኖሚ ቦታዋን ታሻሽላለች ሲሉም አረጋግጠዋል። ይህን ተከትሎም የድህነት ስሟ ይቀለበሳል፤ የርሃብ ስሟ ይቀራል፤ የበለጸገች ፍላጎቷን የምታስከብርና የምታስጠብቅ፣ ከዓለም ስንዴም ሆነ ፍትሕ የማትለምን ሀገር ትሆናለች ነው ያሉት። ከበባው አለ፤ አብሮ ሯጩ አለ፤ ትከሻ የሚገፋፋው አለ፤ በከፍተኛ ፍጥነት በሁሉም ዘርፍ ሮጠን የመጨረሻዋን መስመር ቆርጠን ብልጽግናችንን እናረጋግጣለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።