የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከ500 በላይ የተለያዩ የመኪና ዕቃዎችና 58 የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ከአራት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከ500 በላይ የተለያዩ የመኪና ዕቃዎችና 58 የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ከአራት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ

AMN ነሃሴ 26/2017

በልደታ ክፍለ ከተማ ሦስት ወረዳዎች በጥናት ላይ በተመሰረተ ኦፕሬሽን ከ500 በላይ የተለያዩ የመኪና ዕቃዎችና 58 የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ከአራት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ተከታታይነት ያለው በወንጀለኞችና የተሠረቁ ዕቃዎችን በሚቀበሉ ግለሠቦች ላይ የጥናት፣ የክትትል፣ የምርመራና የኦፕሬሽን ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታዉቋል። መምሪያዉ ከነሐሴ 22 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ/ም በልደታ ክፍለ ከተማ ሦስት ወረዳዎች፤ በወረዳ 3፣ 7 እና 9 የተሠረቁ የመኪና ዕቃዎችንና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን እየገዙ የሚሸጡ ግለሠቦችን በጥናት ለይቷል።

በክፍለ ከተማው ልዩ ቦታው ጌጃ ሰፈር፣ ሱማሌ ተራ እና አብነት አካባቢዎች በተለዩ መኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ላይ የልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የፍርድ ቤት የመበርበሪያና የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት በተጠቀሱት ሦስት ወረዳዎች የተለያዩ የመኪናና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ከሌባ የሚገዙና የሚቀበሉ ግለሰቦች ላይ ኦፕሬሽን ማካሄዱን ገልጿል።

በተከናወነዉ ኦፕሬሽን መሠረት 209 የጎን መስታወት (ስፖኪዮ)፣ 84 ፍሬቻ፣ 6 የፊት መብራት፣ 56 ጌጅ፣ 32 የመኪና ጌጥ፣ 66 ቸርኬ፣ 11 የተሽከርካሪ ዓርማ፣ 7 የኤሌክትሪክ ቻርጀሮች፣ 34 የመኪና ሠሌዳዎች፣ 13 ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 4 ዴስክቶፕ ኮምፒውተር፣ 41 የሞባይል ቀፎዎች እንዲሁም የተለያዩ ሀሠተኛ ሠነዶችን ከአራት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ አስታዉቋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ የማስፋት ተግባሩን እያከናወነ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ የተጠቀሱት የመኪናና የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ተሰርቆብኛል የሚል አካል ልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመምጣት ዕቃውን መለየትና መረከብ እንደሚችል ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታውቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review