የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል በመባል የሚታወቀው በግድብ ከሚያዝ ውሀ የሚመነጨው ሀይል በአለም ላይ ተጠቃሽ ከሆኑ ቀዳሚ የሀይል አማራጮች መካከል አንዱ ነው።
ሀገራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ ኢንዱስትሪዎችን ለማንቀሳቀስ የኒውክሌር ሀይል፣ የድንጋይ ከሰል፣ የንፋስ፣ የጂኦተርማል፣ የጸሀይ እንዲሁም ግድቦችን ለሀይል ማመንጫነት ይጠቀማሉ።
ከአለም 10 ግዙፍ ግድቦች ዝርዝር ውስጥ 4 ግድቦችን ማስመዝገብ የቻለችው ቻይና በግድብ ሀይል ማመንጫ ስኬታማ ስራን መስራት ችላለች።
ከፍተኛ የሀይል እጥረት የሚስተዋልባት አፍሪካ ታዳሽ ሀይሎችን ለማልማት እንቅስቃሴ ቢኖርም ከአህጉሪቷ የህዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ ጥያቄ አንጻር እጅጉን አናሳ ነው።
ኢንተርናሽናል ሀይድሮ ፓዎር አሶሴሽን በአፍሪካ የሚገኙ 10 ግዙፍ የሀይል ማመንጫ ግድቦች በሚል ባወጣው ዝርዝር ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀዳሚ አድርጎታል።
ለምርቃቱ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት ኢትዮጵያውያን ያለማንም ድጋፍ ኪሳቸውን ከፍተው፣ መቀነታቸውን ፈተው የገነቡት ግድብ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ከአፍሪካ ቀዳሚው ነው።
1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ግድብ 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ የመያዝ አቅም ያለው ነው።
በተጨማሪም የዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው በዚህም በሚያመነጨው ሀይል እና በመጠኑ በአፍሪካ ቀዳሚ ከመሆኑ በዘለለ በአለም ላይ ከሚጠቀሱ ግድቦች መካከልም አንዱ ነው ።
ህዳሴ ግድብን ተከትሎ በ1970 የተጠናቀቀው የግብጹ አስዋን ሁለተኛ ሲሆን 2 ሺህ 100 ሜጋዋት ማመንጫት ይችላል።
በዛምቤዚ ወንዝ ላይ የተሰራው ካሆራ ባሳ የተሰኘው የሞዛምቢክ ግድብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፤ ግልገል ጊቤ 3፣ ኢንጋ እና በዛምቢያ እና ዚምባቡዌ አጋርነት የሚተዳደረው ካሪባ ከአራተኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ጎረቤታሞቹ ዚምባቡዌ እና ዛምቢያ የሚያስተዳድሩት ካሪባ ግድብ በአፍሪካ ትብብር ከለሙ ጥቂት ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳል።
እ.ኤእ. በ2009 ወደ ስራ የገባው የሱዳኑ ሜሮዌ 1 ሺህ 250 ሜጋ ዋት በማመንጨት 7ኛ ላይ ሲቀመጥ፤ ተከዜ 8ኛ፣ የጋናው አኮሶምቦ 9ኛ እንዲሁም 760 ሜጋዋት የሚያመነጨው የናይጄሪያው ካይንጂ በ10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ዳዊት በሪሁን