በፊና ፕሮጀክት 14 ግድቦች መገንባታቸው የአርብቶ አደሩን የውሃ እና የመኖ እጥረት እንዲቀረፍ ማስቻሉ ተገለፀ

You are currently viewing በፊና ፕሮጀክት 14 ግድቦች መገንባታቸው የአርብቶ አደሩን የውሃ እና የመኖ እጥረት እንዲቀረፍ ማስቻሉ ተገለፀ

AMN – ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም

በፊና ፕሮጀክት 14 ግድቦች መገንባታቸው የአርብቶ አደሩን የውሃ እና የመኖ እጥረት እንዲቀረፍ ማስቻሉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ ቦረና በነበረን ቆይታ የቦረና አርብቶ አደሮችን ደስታ ማየታቸውን ገልፀዋል፡

የዝናብ እጥረት በተደጋጋሚ በድርቅ እንዲፈተን አድርጎት የነበረው የቦረና ዞን በአዲስ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዞኑ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔን ለማበጀት በተጀመረው ፊና ፕሮጀክት 14 ግድቦች መገንባታቸው የአርብቶ አደሩ የውሃ እና የመኖ እጥረት እንዲቀረፍ ማስቻሉን ተመልክተናል ብለዋል፡፡

ፊና ውሃን፣ መሬትን፣ ግጦሽን ማስተዳደርና ከህይወት ጋር አያይዞ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጡ ማስቻል ነው፤ ይህንን ደግሞ የቦረና ህዝብ በተግባር ማሳየት ችሏል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ዛሬ የቦረና አርብቶ አደሮች የድርቅ ስጋት የለባቸውም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከብቶች በጥጋብ ከመስክ ውለው ይገባሉ፤ ልማት አለ፤ ውሃው አለ፤ መኖው አለ፤ ቦረና ሁሉም ሙሉ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ችግር ብልሃትን ይወልዳል እንዲሉ የቦረና ህዝብ ለሌሎችም ጭምር ምሳሌ የሚሆን ስራ ሰርቷል ያሉት አቶ ተመስገን፤ ይህንን ተግባራዊ ላደረጉ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች እና ለቦረና ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review