መጪው አዲስ ዓመት አምና የነበሩ ድሎች ይበልጥ እንዲሰፉ የሚሰራበት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

You are currently viewing መጪው አዲስ ዓመት አምና የነበሩ ድሎች ይበልጥ እንዲሰፉ የሚሰራበት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

AMN – ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም

መጪው አዲስ ዓመት አምና የነበሩ ድሎች ይበልጥ የሚሰፋበት፣ ተግዳሮቶች የሚቀንሱበት እንዲሆን ሰፊ ዕቅድ መቀመጡንና፤ ይህን መሰረት በማድረግም ወደ ንቅናቄ መገባቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ከነበረችበት አስቸጋሪ የፋይናንስ ውዝፍ ወጥታ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ ተሸጋግራለች ብለዋል፡፡

በታዳሽ ኃይል ማመንጫ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ብንደረግም በድል ተወጥተነዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ በብዙዎች ዘንድ አይችሉም የተባልንበትን ምዕራፍም ዘግተናል ነው ያሉት፡፡

ሥራውን ለማስቆም የተቆፈረውን ጉድጓድ ሁሉ በአመራር ጥበብ እና ብልሃት በተደራጀ የህዝብ አቅም በመታገዝ ማለፍ መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያውያን በደማችን፣ በላባችን እና በአንጡራ ሀብታችን የህዳሴ ግድብን፣ ግዙፉን የአፍሪካ ፕሮጀክት፣ ከለውጡ በፊት ከነበረበት ቅርቃር በማውጣት ማጠናቀቅ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ሀገራችን ከአግድም እና የቁልቁለት ጉዞ ወጥታ የከፍታ ጉዞ የጀመረችበት እና የማንሰራራት ጅማሮ ያሳየችበት ዓመት እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡

2017 በጀት ዓመት ለኢትዮጵያ በእጅጉ ስኬታማ ዓመት እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡

ዓመቱ ውስብስብ ፈተናዎችን በመሻገር በሁሉም ዘርፎች አኩሪ እና እምርታዊ ድሎች የተመዘገቡበት ዓመት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ድሎቹ ብዙ ሊነገርላቸው የሚገባ፣ ትምህርትም የሚቀሰምባቸው እና ለቀጣይ ሀገራዊ ድሎች እንደወረት የሚወሰዱ መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡

መጪው አዲስ ዓመትም እነዚህ ድሎች ይበልጥ የሚሰፉበት፣ ተግዳሮቶች የሚቀንሱበት እንዲሆን ሰፊ ዕቅድ መቀመጡንና ይህን መሰረት በማድረግም ወደ ንቅናቄ መገባቱን ገልጸዋል፡፡

ጳጉሜን ወር የአዲስ ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ተጠናቆ ሥራ የሚጀመርበት የክረምት ወር አልፎ የፀደይ ወቅት የሚጀመርበት እና የአዲስ ዓመት ዋዜማ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የጳጉሜን ቀናትም በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

በዚህም ጳጉሜን 1 የጽናት ቀን፣ ጳጉሜን 2 የሕብር ቀን፣ ጳጉሜን 3 የእምርታ ቀን፣ ጳጉሜን 4 የማንሰራራት ቀን እና ጳጉሜን 5 የነገው ቀን በሚል እንደሚከበሩ ገልጸዋል።

ቀናቱም በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚከበሩ ጠቁመዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review